AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም
በሀረሪ ክልል ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዕውቅና ሽልማት መርሀ ግብር አካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ በአገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በርዕሰ መስተዳድሩ ሽልማት እና የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ የተመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን በመጠቆም የተመዘገበውን ውጤት ለማሻሻል መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተለይ እውቀት፤ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም ለዚህም መሰረቱ የተማረ የሰው ሀይል ቁጥርን ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ያደጉ አገራት ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ መሰረት የጣለው የሰው ሀይላቸውን አልምተው መጠቀም በመቻላቸው መሆኑን በመጠቆም እንደ አገርም ሆነ ክልል ያለውን የሰው ሀይል አልምቶ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በጥሩ ስነ ምግባር የታነፁ ወንድማማችነት እና ትብብርን የሚያውቅ ትውልድ መፍጠር የመንግስት ቀዳሚ ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስት ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰቶ እየሰራ መሆኑን በመጠቆም ተማሪዎችም ከአለባሌ ቦታ በመራቅ ግዜያቸውን በአግባቡ በሚጠቅማቸው ነገር ማሳለፍ እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይ በ2016 የተመዘበውን ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔን ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በተሰራው ስራ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል መቻሉን ጠቁመዋል።
በተለይ በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን በመቀነስ የተማሪዎች የትምህርት ቅበላ እንዲጎለብት ማድረጉን አመላክተዋል።
በ2017 የትምሀርት ዘመንም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያሳያል።