AMN-ታህሳስ 18/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ የሰላም ሰራዊት ብሎክ አመራሮች የማነቃቂያ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም ስልጠናውን ሲከታተሉ ለነበሩ ከ4 ሺህ 9 መቶ በላይ ለሚሆኑ የብሎክ አመራሮች የስራ ስምሪት ተሰጥቷል።
የስራ ስምሪት አቅጣጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ አደረጃጀቱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ ደጀን ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ይህ አደረጃጀት ተለዋዋጭ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶችን መመከት እንዲችል በየጊዜው የንድፈ ሀሳብና የወታደራዊ ስልጠና እንዲወስድ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ስልጠናውን በብቃት ላጠናቀቁ የሰላም ሰራዊት አባላት የዋንጫና ሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቷል።
5 ዓመታት ያስቆጠረው እና ህዝቡን የሰላም ባለቤት የማድረግ ዓላማ ያነገበው የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት በከተማዋ ስርዓት አልበኝነት እና የወንጀል ድርጊቶች እንዲቀንሱ አስተዋፅኦ ስለማድረጉ በመርሐ ግብሩ ላይ ተነግሯል።
በትዕግስት መንግስቱ