AMN-የካቲት 30/2017 ዓ.ም
ለአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ እና ለአገልግሎት መብቃት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኮንቬንሽን ማዕከሉን ሀሳብ ከመጠንሰስ ጀምሮ በግንባታው ሂደትና እስከ ምረቃ ባለው ሂደት በቀጥታም በተዘዋዋሪም አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
“ስንተባበር በጋራ ቆመን የጎደለውን ስንሞላ በሀሳባችን በገንዘባችን አብረን ስንቆም ሀገራችንን ከፍ እናደርጋታለን” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ተባብረን በአንድነት ስንቆም ለስኬት እንደምንበቃ ይሄ ኮንቬንሽን ማሳያ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ያጋጠሙንን ፈተናዎች አልፈን በትጋት ከሰራን ለስኬት እንደምንበቃም ኮንቬንሽኑ ህያው ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል ከንቲባ አዳነች።
ኮንቬንሽኑ ቀደም ብሎ ቢጀመርም ተጓቶ መቆየቱን በማውሳት ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ በማስገንዘብ ትብብር እና አብሮ መስራትን ስንጠይቅ ብዙዎች ትብብር አድርገው የኮንቬንሽን ማዕከሉን ለስኬት አብቅተውታል ብለዋል።
“ስንተባበር በጋራ ስንሆን አቅም እናዳብራለን በቀጣይ ኮንቬንሽኑንም በተሻለ ደረጃ ለማስተዳደር እና በአለም ዙሪያ ለማስተዋወቅና ገበያ ለመሳብ ያለውን እውቀትና ሀብት በማስተባበር መስራት አለብን” ሲሉም ተናግረዋል።
ኮንቬንሽን ማዕከሉ 205 ቢሊየን የተፈቀደ ካፒታል እንዳለው ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች ትልቅ አቅም እና ሀብት በመሆኑ የግሉ ዘርፍ እና የልማት ድርጅቶች አክስዮኑን በመግዛት ባለድርሻ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰብስቤ ባዩ