አጀንዳ 2063 የአፍሪካዊያን አንድነትና ብልጽግና የሚረጋገጥበት የአህጉሩ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ሲሆን የአፍሪካ አህጉር እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2063 ድረስ ለ50 ዓመታት ያክል የሚመራበትን አቅጣጫ የያዘ ነው።
ማዕቀፉ በዋናነት ከሚያካትታቸው ሰባት አላማዎች መካከል፡- ሁሉን አቀፍ በሆነ እድገትና በዘላቂ ልማት የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር፤ በፓን አፍሪካኒም እሳቤዎችና በአፍሪካ ሕዳሴ ራዕይ አማካኝነት የተሳሰረና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው አህጉር እውን ማድረግ፤ የአፍሪካን አህጉር መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ የሰብአዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚከበርበት እንዲሁም ፍትሕ የነገሰበትና ዴሞክራሲያዊ የዳበረበት አህጉር ማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም ሰላሙ እና አንድነቱ የተጠበቀበት፤ ጠንካራ የባህል ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶች ያሉት፣ ማህበረሰባዊ የሞራል መሰረት የፈጠረ፤ በልማት ዜጎችን ማዕከል ያደረገ አፍሪካን መፍጠር፣ የወጣቶችና ሴቶችን አቅም የሚጠቀምና ለሕጻናት ክብካቤ ትኩረት የሰጠ፣ የማይበገርና በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽእኖ ፈጣሪና አጋር የሆነ አፍሪካን መፍጠር የሚሉትም የማዕቀፉ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
የማዕቀፉ የ10 ዓመታት ትግበራ በአህጉሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አምጥቷል፡፡
ለአብነትም በአህጉሩ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል፣ አካታችነት ያለው ገቢ መጨመር፣ የሀገራት የእርስ በርዕስ ግንኙነት እያደገ መምጣቱ፣ የሴቶች፣ወጣቶች እና ህፃናት ተጠቃሚነት ማደጉ እና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የአፍሪካን ሀገራት ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቁ ሁኔታዎች እየጨመረና እየተሻሻለ መምጣቱን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያም አጀንዳ 2063 እውን እንዲሆን የበኩሏን ሚና እያበረከተች ትገኛለች፡፡ ጎረቤት ሀገራትን በሀይል አቅርቦት ለማስተሳሰር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለዚህ አንዱ ማሳያ ሲሆን ይህንን ተግባር እውን ለማድረግም ለተለያዩ ሀገራት የመስመር ዝርጋታ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሀገራት በአየርና በየብስ ትራንስፖርት በማስተሳሰር ረገድም ትርጉም ያላቸውን ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች፡፡ በተለይም ለአፍሪካ ምልክት እና ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በየብስ ትራንስፖርት በኩልም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ድንበር አቋራጭ የአስፋልት መንገዶችን እየገነባች ትገኛለች፡፡
በአጀንዳ 2063 የተቀመጠውን አፍሪካን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግና የታለመውን ለማሳካት ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የገነባቻቸው ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እና የመዝናኛ ማዕከላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የከተሞችን ደረጃ ማሻሻልና የነዋሪዎች ተጠቃሚነት ማሻሻል በአጀንዳ 2063 ከተቀመጡ ግቦች መካከል አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያም ይህን ግብ እውን ለማድረግ የከተሞችን ደረጃ የማሻሻልና የሰው ተኮር ተግባራትን በማከናውን ረገድ ሰፊ ርቀት ተጉዛለች፡፡ ለአብነትም መዲናችንን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት እና ሰው ተኮር ተግባራት ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
ከብከለት የፀዳች አህጉርን እውን ለማድረግ በሚሰራው ስራም ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ቀርፃ ወደ ተግባር በመግባቷ ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማስመዝገብ የቻለች ሲሆን ጎረቤት ሀገራትም ለዚህ በጎ ተግባር የራሳቸውን ሚና ይወጡ ዘንድ የበኩሏን ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ ሴቶችን በማብቃትና ወደፊት እንዲመጡ በማደረግ፣ ወጣቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የአዳዲስ ፈጠራዎች ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ዘመናዊ የሳይንስ ሙዚየም በመገንባት እውቀታቸውን እና ክህሎታቸውን በማሳደግ ለሀገራቸው ብሎም ለአፍሪካ አስተዋጽኦ እንዲያደረጉ በማድረጉ በኩልም ሰፊ ርቀት ተጉዛለች፡፡
ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በሌሎችም ዘርፎች እያስመዘገበቻቸው ያሉ ተግባራት፣ በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦች መሳካት የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በአስማረ መኮንን