ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ እና እግር ኳስ

You are currently viewing ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ እና እግር ኳስ

AMN – ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም

በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ፖፕ ፍራንሲስ ለእግር ኳስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡

ልጅነታቸውን ያሳለፉት በተወለዱባት በአርጀንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ ጎዳናዎች ላይ ከጨርቅ የተሰራ ኳስ እያከባለሉ ነበር፡፡

በብዛት ግብጠባቂ ሆነው ሲጫወቱ ሃሴት ይሰጣቸው እንደነበር ተናግረው ያውቃሉ፡፡

ከትውልድ ከተማቸው ቦነስ አይረስ በመጠኑ ወጣ ብላ በምትገኘው ቦኤዶ በተሰኘች ቦታ መቀመጫውን ላደረገው ሳን ሎሬንዞ ክለብ የነበራቸው ድጋፍ ጥልቅ ነው፡፡

ከአባታቸው ጋር በመሆን ደጋግመው ስታዲየም ገብተው ጨዋታ ተመልክተዋል፡፡

የዓመት ትኬት ተገዝቶላቸው ያለምንም መሳቀቅ የሚወዱትን ክለብ ሳን ሎሬንዞን ጨዋታ ይታደሙም ነበር፡፡

በግልፅ የሳን ሎሬንዞ ደጋፊ መሆናቸውን ይናገሩ እንጂ ሁሉንም ክለቦች በእኩል ዐይን ለማየት ይሞክራሉ፡፡

በተለይ ሊቃነ ጳጳሳት ከሆኑ በኋላ ይህ ተግባራቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የሀገራቸው ሃያል ክለብ እና የሳንሎሬንዞ ተቀናቃኝ ቦካ ጁኒየርስ የአባልነት ካርድ ሲሰጣቸው በይፋ መቀበላቸው ነው፡፡

እግር ኳስ ዓለም ላይ ያለውን ተወዳጅነት ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት ፖፕ ፍራንሲስ ወደ ተለያዩ ሀገራት ሲያቀኑ ሰዎች እንዲሰባሰቡ ይፈልጉ የነበረው በስታዲየም ነው፡፡

እግር ኳስ የሰላም መሳሪያ እንዲሆን ጥረዋል፤ ሁሌም ስፖርቱ የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖ ጎልቶ እንዲወጣም ደክመዋል፡፡

ከጣልያን ስደተኞች በአርጀንቲና የተወለዱት ፖፕ ፍራንሲስ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ቫቲካን ሲከትሙ በርካታ ክለቦችን፣ ብሄራዊ ቡድኖችን እና ተጫዋቾችን ተቀብለው አስተናግደዋል፡፡

ከዲያጎ ማራዶና እስከ ሊዮኔል ሜሲ፤ ከጂያንሉጂ ቡፎን እስከ ማሪዮ ባሎቴሊ ሌሎች በርካቶች የፖፕ ፍራንሲስን ደጅ ረግጠዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱም ምግባረ ሰናዮቹን አበርትተው መለወጥ አለባቸው ያሏቸውን አባታዊ ምክር ሰጥተው አሰናብተዋል፡፡

ክለቦችም ይሁኑ ተጫዋቾች ለፖፕ ፍራንሲስ ለቁጥር የሚታክቱ ስጦታዎችን በተለይ መለያዎችን አበርክተውላቸዋል፡፡

አርጀንቲናዊ እንደመሆናቸው በአንድ ወቅት ’’ማራዶና ወይስ ሜሲ ማንን ይመርጣሉ?’’ ተብለው ሲጠየቁ ’’ማራዶና እንደ እግር ኳስ ተጫዋች ሊቅ ነው፡፡ እንደ ሰው ግን ፈተናውን አላለፈም፤’’ የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

ታላቁ እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌንም ’’ንፁህ ልብ ያለው’’ ብለውት ያውቃሉ፡፡

እግር ኳስ እውነተኛ ወዳጁን አጥቷል፤ ለዛም ነው ቫቲካን ህልፈታቸውን ለዓለም ስታሳውቅ ክለቦች ፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ከማንም ቀድመው ሃዘናቸውን የገለፁት፡፡

በትንሳኤ ማግስት በ88 ዓመታቸው ያረፉት ፖፕ ፍራንሲስ በእግር ኳሱ ዓለም ያላቸው የገዘፈ ምስል ለዓመታት ጎልቶ መታየቱ አይቀርም፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review