AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም
የልማት ተነሺዎች ምቹ የመኖሪያ እና የሥራ ቦታ እንዲኖራቸው ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገልጿል፡፡
የመሬት ማስተላለፍ እና ዝግጅት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ደስታ መርጋ፣ የኮሪደር ልማት ስራው የከተማ አስተዳደሩ ዋና ተግባር ቢሆንም የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮም ትልቅ የስራ ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ስራ ሰፊ የስራ ድርሻ ያለው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ልክ እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ በሁለተኛውም ዙር የተጣለበትን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ እየተወጣ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
በቢሮው የመሬት ማስተላለፍ እና ዝግጅት ዘርፍ ከክፍለ ከተሞች ጋር የስራውን አሁናዊ ገፅታ ገምግሟል፡፡
በግምገማ መድረኩ እንደተገለጸውም፣ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በወሰን ማስከበር፣በይዞታ ማረጋገጥ፣ በመሬት ዝግጅት እና ካርታ ዝግጅት ስራዎችን በየጊዜው በመገምገም የልማት ተነሽዎች ምቹ የመኖሪያና የሥራ ቦታ እንዲኖራቸው ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የከተማ አስደተዳደሩን ዕቅድ በመደገፍ እና የልማቱ አጋዥ በመሆኑ ከመኖሪያና ከስራ ስፍራቸው የሚነሱ ዜጎችን በተገቢው በማስተናገድ ምቹ የመኖሪያና የስራ ቦታ እንዲኖራቸው ማስቻል የኛ ዋነኛ ተግባር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ተግባሩ የተለየ ትኩረትን ይሻል ያሉት ኃላፊው፣ የልማት ተነሽዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ስራዎቻችንን በቅንጅት መስራት ይኖርብናል በማለትም ተናግረዋል፡፡
ከመረጃ ውስንነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍም ቀሪ ስራዎች ባጠር ጊዜ እንዲጠናቀቁ መረባረብ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ይህንንም ስራ በበላይነት የሚመራ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጥ ቡድን በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉንም የቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡