ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

AMN – ታኅሣሥ -2/2017 ዓ.ም

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸውን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ሰርቲፊኬት እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከፌዴራል አካባቢ ባለስልጣን ጋር ተፈራርሟል።

የመግባባቢያ ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሚ ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በኮርፖሬሽኑ ስር የሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለማድረግ አንዱ የአካባበቢ ጥበቃ ስራን ከግምት ውስጥ ያስገባ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እና መተግበር እንዲሁም ስራውን በዲሲፕሊን መምራት መቻል በመሆኑ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ፍስሃ በተጨማሪም የስፔሻል ኢኮኖሚ ዞኖች የአረንጓዴ አፈጻጸም ተግባራትን በኢኮ- ኢንዱስትሪያል ፓርክ ፅንሰ ሃሳብ መሠረት የአረንጓዴ ምስክር ወረቀት ዉስጥ መግባታቸው ለስራ ምቹ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ከማድረጉ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር እና በሃገር ደረጃ ለተያዘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሚ በበኩላቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈረሙት የአካባቢ ጥበቃ ህጎች መሰረት ያሉበትን ደረጃ በመመዘን ያሟሉትን እውቅና ለመስጠትና ክፍተት ያለባቸውን ደግሞ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመተባበር ደረጃውን እንዲያሟሉ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ በሃይል እና በውሃ አጠቃቀም እንዲሁም በተረፈ ምርት አወጋገድና ቅነሳ በሁሉም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የተሰሩትን ስራዎች በመመዘን እውቅና ለመስጠት ያለመ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመትም 4 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በመመዘን እውቅና የሚሰጥ መሆኑ በስምምነቱ ስነ-ስርዓቱ ወቅት መገለፁን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review