ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን በአብሮነትና በመረዳዳት በጋራ ማሳለፍ እንደሚገባው የኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሀፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፖስተር ጻድቁ አብዶ የትንሳኤ በዓልን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በመግለጫቸው፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር በድንበር ለተሰማሩ ወታደሮች፣ በተለያዩ የዓለማት ክፍል ለሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮችና ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የትንሳኤ በዓል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ፍቅሩን የገለጸበት ትህትናን ያስተማረበት መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በዓሉን ስናከብር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት በመጸለይ እንዲሁም የተቸገሩትን በመርዳት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በዓሉ ለተቸገሩት ካለን የምናካፍልበት እና አብሮነታችንን የምናሳይበት ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የትንሳኤ በዓል የትህትናና የመከባበር እሴታችንን የምናሳይበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ትንሳኤ ጥላቻ በፍቅር፤ መለያየት በአንድነት፣ ሐዘን በደስታ የተቀየረበት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍቅር የተገለጠበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም በመላው ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች ለተከፉ ለተከዙ ወገኖች የደስታ ምንጭ በመሆን አብሮነታችንን ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሀፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ የትንሳኤን በዓል ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በማሳለፍ የክርስቶስን ፍቅር ማሳየት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የካውንስሉ ጠቅላይ ጸሀፊ በመግለጫቸው የትንሳኤን መታሰቢያ በዓል ስናከብር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር አንድያ ልጁን አሳልፎ እንደሰጠ በማስታወስ ነው ብለዋል፡፡
ትንሳኤ የተጣሉ የሚታረቁበት፤ የተራራቁ የሚቀራረቡበት እንዲሆን ታርቆ በማስታረቅ መልካም ምሳሌ መሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ሰላም እና የህዝቦቿን አንድነት በጽኑ ዓለት ላይ ለማቆም በመከባበርና መደማመጥ ላይ የተመሰረተ ውይይትና እርቅ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፖስተር ጻድቁ አብዶ፤ የትንሳኤን በዓል በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ድረስ ያደረጋቸው ተግባራት ለእኛ ለሰው ልጆች ትህትናና ፍቅርን የሚያስተምሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ክርስቶስ ለእኛ የከፈለውን መስዋዕትነት በማሰብ ምዕመናን የተራቡትን በማብላት የተጠሙትን በማጠጣት የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት ማሳላፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ምዕምናን የትንሳኤ በዓልን ለኢትዮጵያውያን አንድነትና ዘላቂ ሰላም በመጸለይ እንዲያከብሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡