AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
ሕጎች ሲወጡ ቅድሚያ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስገኙት ጥቅም በግልጽ ታውቆና ተፈትሾ ሊሆን እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
አፈ-ጉባኤው ይህንን ያስገነዘቡት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለአማካሪ እና ለአስተባባሪ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።
ኮሚቴዎች ሕጎችን የሚመረምሩበት የድርጊት መርሐ-ግብር መቀመጥ እንዳለበት አፈ ጉባኤው በዚህ ወቅት አመላክተዋል።

ቋሚ ኮሚቴዎች ሕጎች ከወጡ በኃላ አፈፃፀማቸውን መከታተልና ለህብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸው አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አካታች የሀገራዊ ምክክር በማድረግና የሽግግር ፍትህ ሥርዓቱን በሁሉም አካባቢዎች በመተግበር የኢትዮጵያን ሠላም ለማፅናት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ምክር ቤቱ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በህዝብ ውክልና ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን እንዳከናወነ ጠቅሰዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተሻለ አፈጻፃም ማሳየቱን ገልጸው፤ በክፍተት የታዩትን በቀጣይ ማስተካከያ ለማድረግ ሁለንተናዊ ጥረት የሚደረግ መሆኑን መናገራቸውን የምክርቤቱ መረጃ ያመላክታል።