AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሀገሪቱ በሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች ዙሪያ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችና ሚዲያዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው የመረጃ ተደራሽነት ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዮናስ ፋንታዬ መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን በችግሩ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን በሚያስተላልፏቸው ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች መስማት የተሳናቸውን ዜጎች በምን መልኩ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን መፈተሽ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ውስን የመገናኛ ብዙሃን በሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች መስማት የተሳናቸው ወገኖች መረጃ እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ቢያቀርቡም በጠቅላላው ሲታይ ብዙ እየተሰራበት አለመሆኑን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች ዙሪያ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን ልዩ ትኩረት ለሚሹ ወገኖች ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡ ለማስቻል ባለስልጣኑ ለዘርፉ ተዋናዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በውይይቱ የተገኙት የህግ ባለሙያው ካልአዩ አያሌው በበኩላቸው በሀገር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ላይ መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የሚሰጡበት ሁኔታ የሚበረታታ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።
ይህ ችግር እንዲቀረፍ መገናኛ ብዙሃን ከምንጊዜውም በላይ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የሚያገኙበትን አካታች ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።