AMN – መጋቢት 7/2017 ዓ.ም
በቦሌ ክፍለ ከተማ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ (DPO) የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እና የሥራ ፕሮጀክት የተለዩ ተጠቃሚዎች ሥራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እና የሥራ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እንዲሁም በሥራ መሠማራት ለማይችሉ ወገኖች በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በክፍለ ከተማው በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የተለዩ ተጠቃሚዎች በትጋት በመሥራት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመለወጥ መጣር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በ119 ወረዳዎች በሚገኙ 803 ከላስተሮች 154ሺህ 923 ተጠቃሚዎች መለየታቸውን ገልጸው፣ እነዚህ ተጠቃሚዎች በአካባቢ ጽዳት፣ በከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እና መሰል ዘርፎች ተሠማርተው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት እንዲሁም የወረዳዎች አመራሮችና ፈጻሚዎች ለልየታው መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ዳዲ፣ በቀጣይ ለፕሮጀክቱ መሳካት የተለመደ ቅንጅታዊ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከመንግሥት በተመደበ ገንዘብ ለሦስት ዓመታት በሚካሄደው ፕሮጀክት በክፍለ ከተማው 3ሺህ 256 አባወራዎችና እማወራዎች እንዲሁም በሥራቸው የሚገኙ 10ሺህ 671 ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለጹት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ኃይሌ፣ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ውጤታማ ለመሆን መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ማስገንዘባቸውን ከክፍለከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡