AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
ለፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት መተግበር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናገሩ።
ከ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በአፍሪካ ህብረት የተመራው እና ትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ከረዳው የሰላም ስምምነት የተቀመሩ ተሞክሮዎች ሪፖርት ቀርቧል።
የሰላም ስምምነት ሂደቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው የህብረቱ መርህ መሰረት የሰላም ንግግሩ በአፍሪካ ህብረት ሙሉ በሙሉ መመራቱ ትልቁ ስኬት እና ተሞክሮ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ግጭቱን ለማስወገድ ተቀናቃኝ ወገኖቹ ሙሉ ቁርጠኝነት ማሳየታቸው እና በባለቤትነት መንፈስ መስራታቸው ፣ የተመረጡ አደራዳሪዎች ልምድ እና ቁርጠኝነት ያላቸው መሆናቸው፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራር፣ ታዛቢዎች ለድርድሩ ስኬት ያልተቋረጠ እገዛ ማድረጋቸው፣ ድርድሩ የፋይናንስ ተግዳሮት እንዳይገጥመው በአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ መደረጉ በተሞክሮነት ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም የድርድሩ ቦታ ሆና የተመረጠችው ደቡብ አፍሪካ ድርድሩን ለማካሄድ ምቹ እና ገለልተኛ መሆኗ እንዲሁም መሪዎቹ ለስኬቱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ በድርድሩ ትክክለኛ ተደራዳሪዎች መወከላቸው፣ በአፍሪካ ህብረት የተወከሉ ልዑካን ሂደቱን በተገቢ መንገድ መምራታቸው፣ ተኩስ ማቆም እና ጸብ አጫሪ ተግባራትን ማቆም ቅድሚያ የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸው፣ በስተመጨረሻም የሰላም ስምምነት መፈረሙ ምርጥ ተሞክሮ ሆነው ከቀረቡት መካከል ተጠቅሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በፕሪቶርያው ስምምነት በተቀመጠው መሠረት የኢትዮጵያን ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ባከበረ መልኩ የፕሪቶርያ ስምምነት በራሳችን በኢትዮጵያውያን ጥረት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለፕሪቶርያው ስምምነት አተገባበር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ጌዲዮን ለትግራይ ክልል በጀትን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌደራል መንግስት ተወካዮች፣የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የክልሉ አመራሮች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ልዑካንና የተለያዩ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በሰብስቤ ባዩ