
መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተለያዩ ግዙፍ ማህበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለማሟላት እያደረገው ያለው ጥረት የሚበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ጤና ተቋማት የሚሰሩ የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች በከተማዋ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዘዋዉረዉ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱም ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን እና እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እነዚህም ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራዎች መሆናቸው በተደረገው ገለፃ ተመላክቷል፡፡
መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ቅድመ መከላከል እና አክሞ የማዳን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
የጉብኝቱ ዋና ዓላማም በተለይም የጤና ተቋማት ተደራሽነትና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ማሳያ መሆናቸውን በመገንዘብ የጤና ባለሙያዎች ሚናቸው የጎላ በመሆኑ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም እነዚህ በርካታ የልማት ስራዎች በ24/7 የስራ ባህል በፍጥነትና በጥራት የተገነቡበትና የታደሱበት እንዲሁም ሰፊ የስራ እድል የተፈጠረባቸው በመሆናቸው ሁሉም ከዚህ ልምድና ተሞክሮ ወስዶ በተሰማራበት የሙያ መስክ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑንም ያለመ ነው ተብላል፡፡

የጤና አመራሮች እና ባለሙያዎች በጉብኝታቸው መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተለያዩ ግዙፍ ማህበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለማሟላት እያደረገው ያለው ጥረት የሚበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ልማቱ በሙያችን ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም ስራ ይበልጥ እንድንሰራ አነሳስቶናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በማሬ ቃጦ