የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እና ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ብሔራዊ የኮምኒኬሽን ስትራቴጂና የጋራ የአምስት ዓመት መሪ እቅድ ይፋ አድርገዋል።
በዕለቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ መንግስት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመቀነስና ዜጎች ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ቀን ይፋ የተደረጉት ብሔራዊ ኮምኒኬሽን ስትራቴጂና በሚኒስቴሩ እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት መካከል የተፈረመው የአምስት ዓመት መሪ እቅድ የፍልሰት አስተዳደርን ውጤታማና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችሉ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም ህብረተሰቡን ማእከል ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን፣ የተጎጂዎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን ማጠናከር እና ለፖሊሲ አውጪዎች አስተማማኝ መረጃ ለማቅረብ፣ የፍልሰት መረጃን ለማደራጀትና ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚያስችሉ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ብሔራዊ የኮምኒኬሽን ስትራቴጂው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መከላከልና እና መደበኛ ፍልሰትን በማበረታታት፣ የፍልሰት መንስኤዎችንና የሚያስከትሉትን ችግሮች በማስገንዘብ የተሻሻለ የኑሮ አማራጮችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው፣ ይፋ የተደረጉት ሁለቱ ሰነዶች በቅንጅት በመስራት በፍልሰት አስተዳደሩ ውጤታማ ከማድረግ አንፃር ስኬትን የሚያስመዘግቡ እንደሆኑ መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡