መገናኛ ብዙሃን ልጆችን በመስራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው – ምሁራን

You are currently viewing መገናኛ ብዙሃን ልጆችን በመስራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው – ምሁራን

AMN- መጋቢት 18/2017 ዓ.ም

መገናኛ ብዙሃን ልጆችን ከመሥራት አኳያ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በይዘት ዘርፍ ጥራት፣ ተነባቢነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነትን ለማሳደግ ያለመ የአርታኢያን መድረክ ተካሂዷል።

ድርጅቱ “ብላቴናት” የተሰኘውን የልጆች መፅሔት ለ9ኛ ጊዜ ያሳተመ ሲሆን፣ በቅርቡም “ናኦታ” በሚል በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ እትሙን አስተዋውቋል።

በመርሃ ግብሩ የፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላት፣ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አካላት፣ የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ከመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት የተጋበዙ ተገኝተዋል።

በመድረኩ የስነ ልቦና ባለሙያ ብሩክ ገብረማሪያም፣ “ብላቴናት መፅሔት ከልጆች ስነ ልቦና አንፃር” በሚል ፅሑፍ አቅርበዋል።

ባለሙያው በፅሑፋቸው፣ አሁን ገበያ ላይ የሚገኙ የልጆች መፅሐፍት በአብዛኛው ያለ በቂ ግንዛቤ እና ስነ ልቦናዊ መርሆዎች የሚዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“ብላቴናት” መፅሔት ግን የልጆችን ዋና ዋና ስነ ልቦናዊ መርሆዎች አሟልቶ የተዘጋጀ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር መኩሪያ መካሻ (ረዳት ፕ/ር) “ብላቴናት መፅሔት አዘገጃጀት ከጋዜጠኝነት አንፃር ” በሚል ርዕስ ፅሑፍ አቅርበዋል።

መፅሔቱን በዳሰሱበት ፅሑፍም፣ መፅሔቱ ከአጠቃላይ ከዲዛይን እና አቀራረብ አንፃር ሳቢ እና የተሟላ ሆኖ የቀረበ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ዲዛይንና ሥነ ውበት፣ ኤዲቶሪያል ይዘት፣ ስዕሎችና ፎቶዎች፣ አጫዋች ይዘቶች፣ ህትመት፣ ፕሩፍ ሪዲንግ እና ኦንላየን ላይ ከመገኘት ጋር በተያያዘ መፅሔቱ በጥሩ ይዘት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሳፍንት ተፈራ፣ መፅሔቱ ከይዘት አኳያ በጥራት ለማዘጋጀት ጥረት እንደተደረገ በማንሳት ከመድረክ እና ከታዳሚያን የተሰነዘሩ ሀሳቦችንም እንደ ግብዓት እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።

ከተደራሽነት አንፃርም በትኩረት እየተሰራ እንዳለና እንደሚሰራም ነው ያመላከቱት።

በኢትዮጵያ የልጆች መፅሐፍት መዘጋጀት ከጀመረ መቶ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን እድገቱ አዝጋሚ እንደሆነ ተገልጿል።

ልጆች በዲጂታል ሚዲያ በመጠመድ ሊደርስባቸው ከሚችል አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለማላቀቅ የህትመት ሚዲያው ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተገለጸው።

መገናኛ ብዙሃንም ልጆችን ከመሥራት አኳያ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑ ተመላክቷል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review