ሙስሊም ስፖርተኞች በረመዳን ወር

You are currently viewing ሙስሊም ስፖርተኞች በረመዳን ወር

ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት መካከል አንዱ  የረመዳን ጾም፣ ጸሎት ወር ነው፡፡ በረመዳን ወር እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የእምነቱ ተከታዮች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ መፆም ደግሞ እስላማዊ ግዴታ እና ፈጣሪን መቅረቢያ ኃይማኖታዊ ክዋኔ ነው፡፡

እንደ እግር ኳስ ያሉ ስፖርታዊ ውድድሮች በሥራ ጠባያቸው ብዙ ላብ የሚፈስበት፤ በዚያው መጠን ያወጡትን ላብ እየተኩ የሚንቀሳቀሱበት ነው። በረመዳን ወር ደግሞ መጾም ግድ በመሆኑ ለሙስሊም ስፖርተኞች ከአካል ብቃት ጋር ተያይዞ የሚፈትናቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን አብዛኞቹ ሙስሊም የእግር ኳስ ተጫዋቾች አካላዊ ድካማቸው በፆማቸው ከሚያገኙት መንፈሳዊ እርካታ ጋር እንደማይነፃፀር ይገልፃሉ፡፡ ለአብነትም የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና የአርሴናል አማካዩ ጀርመናዊው ሜሱት ኦዚል “በረመዳን ወር እግር ኳስ መጫወትን፣ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት እና መፆምን ፈልጌ የማደርጋቸው ናቸው” ብሏል፡፡

ዘመናዊ የእግር ኳስ ብዙ ልምምድ፣ ያወጡትን መተካት እና እረፍትን ግዴታ ያደርጋል፡፡ ታድያ የረመዳን ጾም ሲመጣ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ጾማቸውንና ስራቸውን ጎን ለጎን የማስኬድ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ስፖርተኞች የጾሙን ድካም እና የውሃ ጥሙን ችለው ብዙ ጊዜ በተሻለ ብርታት ሥራቸውን ሲወጡ ይታያል፡፡ ሆኖም ልምምድ አልፎ በተለይ አመሻሽ ላይ ግጥሚያዎች ሲደረጉ የኢፍጣር ሰዓት የሚደርሰው ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ባሉበት ይሆንና ሌላ ፈተና ይደቅንባቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍም በእስልምና አማኞች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን የረመዳን ወር መጀመሩን አስመልክተን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን የሙስሊም ስፖርተኞችን በተለይም የእግር ኳስ ተጫዋቾችን የረመዳን ወር ክራሞት በአጭሩ እንቃኛለን፡፡

የቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሙኤዝ ሀሰን በፈጠረው ዘዴ ጨዋታው ሳይቋረጥ ወይም ዳኛው ፍቃድ ሳይሰጡ ፆማቸውን እንዲፈቱ ያደረገበት አጋጣሚ በዚህ ረገድ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ሩሲያ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ላይ የፖርቹጋል እና ከቱርክዬ ብሔራዊ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ላይ ነበር ክስተቱ የተፈጠረው፡፡ ሙስሊም ተጫዋቾች የፆም መፍቻ ሰዓታቸው (የአፍጥር ሰዓት) ሲደርስ የቱኒዚያው ግብ ጠባቂ ሙኤዝ ሀሰን የሰዓት መድረስ ጠብቆ በእግሩ ላይ ጉዳት የደረሰበት በማስመሰል ዳኛው ሐኪሞች ገብተው እንዲረዱት ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉ አስገድዷቸዋል፡፡ በወቅቱ ከቱርክዬ ጋር ሲጫወቱ እንደዚሁ ትከሻው ላይ ጉዳት ያጋጠመው አስመስሎ ዳኛው የሕክምና አባላትን ወደ ሜዳ ለመግባት እንዲያዙ የተለመደ ዘዴውን ተጠቅሟል፡፡

ግብ ጠባቂው ሙኤዝ ሀሰን ሜዳ ላይ እየወደቀ የሐኪሞችን እርዳታ በሚያገኝበት ወቅት የቱኒዚያ እና የተፋላሚያቸው ሙስሊም ተጫዋቾች አፍጥር ያደርጋሉ፡፡ ፆማቸውን የሚፈቱት ግን ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊም የሆኑ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ሌሎችም ባለሙያዎች ጭምር ነበሩ። የግብ ጠባቂው ዘዴ በወቅቱ ሕግ ያልወጣለትን የሙስሊም ተጫዋቾች የማፍጠሪያ ጊዜ በዘዴ ያስገኘ ሆኖ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡

ከሞሮኮ አባቱ እና እንግሊዛዊ እናቱ ጋር በለንደን ያደገው የውሃ ላይ ቀዛፊ ስፖርተኛ ሞ ስቢሂ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ እንደሚያስረዳው የረመዳን ወር ላይ ልዩ ስሜት አለው። ነገር ግን በዛኑ ልክ አድካሚውን ስልጠናና ውድድሮችን ስለሚያደርግ በትንሹም ቢሆን መፈተኑ እንደማይቀር ያስረዳል፡፡ ይሁንና “ምንም እንኳን አድካሚ ሁኔታ ላይ ብሆንም መጾሜን አላቋርጥም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜም ቢሆን ፈታኝ ውድድር ሲኖርብኝና ድካም ሲሰማኝ የማቋርጥበት ቀናት አሉ፡፡”

ጾሜን ካቋረጥኩ ግን አደረግዋለሁ ያለውን ለዘ ጋርዲያን ሲየስረዳ “በሰሜን አፍሪካ ውስጥ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለሚረዳው ዋሎውዩስ ለተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት እና በሞሮኮ ላሉ ችግረኛ ቤተሰቦች ገንዘብ እየሰጠሁ አካክሳለሁ“ ብሏል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና በተቀሩት ሦስቱ የእንግሊዝ እግር ኳስ ውድድሮች ውስጥ በሚሳተፉ ክለቦች እና አካዳሚዎቻቸው ውስጥ በአጠቃላይ 253 ሙስሊም ተጫዋቾች እንዳሉ ከዓመት በፊት ሊጉ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኤቨርተኑ አማካይ አብዱላዬ ዱኩሬ ይገኝበታል። ተጫዋቹ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ እንደተናገረው “ረመዳንን ሁሌም እወደዋለሁ” ሲል ተናግሯል። “አንዳንድ ጊዜ በፀደይ ወቅት ይሆን እና ውድድር ከመጀመሩ በፊት ስለምንፆም ትንሽ ይከብዳል። ነገር ግን እኔ አንድም ጊዜ ችግር ስላላጋጠመኝ ዕድለኛ ነኝ፣ እምነቴ በሕይወቴ በጣም አስፈላጊው ነገር ነው” ይላል ዱኩሬ።

በመልበሻ ክፍል ከሌሎች እስልምና ተከታይ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ፀሎት ያደርጋል፣ ዘወትር አርብ ደግሞ ጁምአን አብረው ያሳልፋሉ። “በፕሪሚየር ሊጉ ሕይወትህን እንደፈቀድክ መኖር ትችላለህ። ማንም በእምነትህ የሚመጣ የለም።” የሚለው ዱኩሬ፣ በረመዳን ወቅት አንድም ቀን ሳልዘል ነው የምፆመው፤ የኤቨርተን ሥነ-ምግብ ክፍል ኃላፊ ሎይድ ፓርከር ተጫዋቾቹ እምነት እና ባሕላቸውን በማይነካ መንገድ ካርቦሃይድሬት (ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግብ) አብዝተን እንድንመገብ ያደርገናል ሲልም ተደምጧል።

ንጋት አካባቢ ፆም ከመጀመሩ በፊት ገንፎ፣ እንቁላል አሊያም ዳቦ በማርማላትና ጭማቂ ይመገባሉ። ከፆም በኋላ ደግሞ በሚንስትሮን ሾርባ ይጀምሩና ፓስታ አሊያም ሩዝና ፍራፍሬ ይታከልበታል። በረመዳን ወቅት ሥልጠና አይጓደልም የሚለው ዱኩሬ፣ የክለቡ ሼፍ ሁሉንም አዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል።

አብዛኛውን የእግር ኳስ ሕይወቱን በቱርክዬ ክለቦች በመጫወት ያሳለፈው የቀድሞ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ የነበረው አብዱል ዘሀር ኤልሳቅ ለብሔራዊ ቡድኑ 112 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ይሄው ግብፃዊ ተጫዋች ደግሞ “በረመዳን የፆም ወር ከሌላው ጊዜ በተሻለ እግር ኳስን እጫወታለሁ፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የፈጣሪዬ እገዛ ስለሚታከልበት ይመስለኛል” በማለት የረመዳን ወር ለሙስሊም ተጫዋቾች የደስታ ወር መሆኑን ገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ በ2021 ክሪስታል ፓላስ ከሌስተር ሲቲ ጋር ባደረጉት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ እንግሊዛዊው ዳኛ ግርሃም ስኮት ጨዋታው በ34ኛው ደቂቃ ላይ እንዲቋረጥ ፊሽካቸውን ነፍተዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የሌስተር ሲቲው ተጫዋች ዌስሊ ፎፋና ‘አፍጥር’ የሚያደርግበት (ፆሙን የሚፈታበት ሰዓት) በመድረሱ ነው፡፡ ዳኛው ጨዋታውን ባስቆሙበት ፍጥነት ዌስሊ ፎፋና ወደ ሜዳው መስመር በመሄድ ፆሙን እንዲፈታ አስችለውታል።

ይህ የዳኛ ግርሃም ስኮት ተግባር የክሪስታል ፓላስ እና የሌስተር ሲቲ ደጋፊዎችን ምስጋና አስገኝቶላቸዋል። በርካታ ሙስሊም የሆኑ እና ያልሆኑ ተጫዋቾችም ለዳኛው አድናቆታቸውን አቅርበዋል፡፡ በዕለቱ ከዳኛው ፍቃድ አግኝቶ ፆሙን የፈታው ዌስሊ ፎፋናም የእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ለኃይማኖቱ የሰጡትን ክብር ከልቡ አመስግኖ ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን በትዊተር ያሰፈረው ፎፎና “እግር ኳስን የተለየ የሚያደርገው ይሄ ነው” ብሏል፡፡

በ2021 እ.ኤ.አ አብዛኛዎቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ከአምበሎች ጋር በመነጋገር የማፍጠሪያ ሰዓት ከደረሰ ኳስ በእጅ ሊወረወር ወይም ከማዕዘን ሊሻማ ሲል ፆማቸውን የሚፈቱ ሙስሊም ተጫዋቾች ፆማቸውን እንዲፈቱ ኳስ ወርዋሪው ወይም ማዕዘን ምት መቺው አውቀው ኳስ እንዲያዘገዩ ሕጋዊ ያልሆነ ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሙስሊም ተጫዋቾት ኳስ በእጅ ሊወረወር ሲል እና ከማዕዘን ሊሻማ ሲል በፍጥነት ፆማቸውን ፈትተው ወደ ጨዋታቸው ይመለሳሉ፡፡

በመላው ዓለም በርካታ ሚሊዮኖች የሚከታተሉት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ዓመት በፊት የረመዳን ወር የሚጾሙ ሙስሊም ተጫዋቾች በሚሳተፉባቸው የአመሻሽ ጨዋታዎች ላይ የኢፍጣር ሰዓት ሲደርስ ዳኞች የጨዋታው ሒደት ሳይስተጓጎል ተጫዋቾች የሚያፈጥሩበትን የአፍታ እረፍት እንዲሰጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል። በዚሁ መሠረት ዳኞች የኢፍጣር ሰዓት መግባቱን ሲያረጋግጡ ኳስ ወደ ውጭ ሲወጣ ጠብቀው ተጫዋቾች እንዲያፈጥሩ ማለትም ውሃ፣ ኢነርጂ ጄል አልያም ሌላ ተመሳሳይ ነገር እንዲወስዱ ዕድል ይሰጣሉ፡፡

ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎች በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ ስፖርተኞች ጉልበት በሚያዝለው እግር ኳስ ከእምነታቸው ሳይጎድሉ አድካሚውን ስራ ተቋቁመው ለስኬት በቅተዋል ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review