ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲታወስ

You are currently viewing ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲታወስ

በጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ሂደት ውስጥ ጎልተው ከሚነሱ አበይት ጉዳዮች መካከል ለመብትና ነጻነት የተደረጉት ትግሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ቅኝ አገዛዝ እንዲያበቃ፣ ባርነት እንዲቀር፣ ጥቁሮች በሚኖሩበት ሀገር እንደ ዜጋ እንዲታዩና መብታቸው እንዲከበር ለብዙ ዓመታት ትግል አድርገዋል፡፡ ለአብነትም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያደረጉትን ተጋድሎ፣ በፈረንጆቹ 1920ዎቹ ጥቁሮች በአሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ ያደረጉትን የሃርለም እንቅስቃሴ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት አገዛዝ እንዲያከትም የተደረጉትን ተጋድሎዎች፣ በፈረንጆቹ 1950 እና 1960ዎቹ በአሜሪካ የተደረጉት የሲቪክ መብቶች እንቅስቃሴ… የጥቁር ህዝቦች የተጋድሎ ታሪክ የተጻፈባቸው አሻራዎች ናቸው፡፡ በዚህ አምድም በወርሃ የካቲት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚታሰበውን “የጥቁሮች ታሪክ ወር”ን (Black History Month) መነሻ በማድረግ የዕውቁ የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግን (ጁኒየር) የህይወት መንገድ፣  ለጥቁር ህዝቦች የዋለው ውለታና በጎ ተግባሮቹን ዳስሰናል፡፡ በዚህ ዓምድ ላይ የተጠቀሱት ቀናት በሙሉ በአውሮጳውያን አቆጣጠር ናቸው፡፡

ሩቅ አሳቢው ህልመኛ

በታህሳስ 1865 የአሜሪካ እርስ በርስ ጦርነት ከተቋጨ በኋላ ባርነት ማብቃቱ ቢታወጅም፣ የጥቁሮች ህይወት ግን በተጨባጭ ከባርነት የተለየ አልነበረም። የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መገለልን ጨምሮ፤ የጥቁሮችን መብት የሚገፍፉ ተቋማዊ አድልኦ እንደቀጠለ ነበር፡፡ በዚህም ጥቁሮች እንደ ሁለተኛ ዜጋ  ይቆጠሩ ነበር። መደበኛ ሥራ ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ የመምረጥና የመመረጥ መብት ተነፍጓቸዋል። ጥቁሮች ከነጮች ጋር በአንድ ትምህርት ቤት የመማር፣ ምግብ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት፣ የህዝብ ትራንስፖርት የመሳሰሉትን መጠቀም አይፈቀድላቸውም ነበር። በአጠቃላይ ዛሬም ድረስ ቅሪቶቹ በተለያየ መንገድ የሚንፀባረቁት አድሎዓዊ ሁኔታዎች፣ ማርቲን ሉተር ኪንግና መሰሎቹ በኖሩበት ዘመን ህጋዊ ሽፋን ያገኘ ድርጊት ነበር።  ማርቲን ሉተር ኪንግ የተቃወመው ይህን መሰል የዘረኝነትና የአድልዖ ስርዓት ተወግዶ በህግ ፊት እኩል የመታየትን ህልም በመሰነቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነው፤ የጥቁር ህዝቦች ተስፋ በደበዘዘበት በዛች ወቅት ተስፋን በመሰነቅ እንደ ትንቢት የሚታየውን  “ሕልም አለኝ” የሚለውን ታሪካዊ ንግግር በፈረንጆቹ 1963 ያደረገው፡፡

ማርቲን ሉተር በዚህ ዝነኛ ንግግሩ ላይ እንዲህ አለ፤ “ሕልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን አራቱ ልጆቼ እንደአሁኑ በቆዳቸው ቀለም፣ በዘር ሃረጋቸው፣ ወይም በፀጉራቸው ሳይሆን፤ በውስጣቸው በያዙት እና አውጥተው በሚያንፀባርቁት የባህርይ ታላቅነት ወይም መጥፎ ባህርይ ብቻ ማንነታቸው የሚመዘንበት የነፃነት ቀን እንደሚመጣ ሕልም አለኝ፡፡”…

ይህ ንግግር በታሪክ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ ንግግሮች መሃል አንዱ ነው ይላል፤ ዘ ኪንግ ሴንተር ገጸ- ድር በ2006 ባስነበበው ሃተታ። ንግግሩ ውስጥ አንዳች ሃይል አለ፡፡ ተበድሎ ይቅር ማለትን፤ ተገፍቶ ርህራሄ ማሳየትን፤ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ቢኖሩም ተስፋ መሰነቅን የሚያስተጋባ ሃይልነት ያለው ትንቢታዊ ንግግር ነው። እንዲሁም የማርቲን ሉተር ንግግር ለዓመታት ጥቁሮችን ከሰውነት ደረጃ ዝቅ የሚያደርጉ መዋቅራዊ ስርዓቶች  ከአሜሪካ ምድር ተሽረው ፍትህ የሚሰፍንበት ዕለት እንደሚመጣ ተስፋ የሚያደርግ ነበር፡፡ ይህ ንግግር በወቅቱ ከነበረው የአሜሪካ ማህበረ-ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር በድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ ሆኖ አንዳች ብልጭታ ብርሃንን ለማየት ተስፋን እንደመሰነቅ የሚቆጠር እንደነበር የገጸ-ድሩ መረጃ ያሳያል፡፡

የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ

በ1998 ‘The Autobiography of Martin Luther King, Jr.’ በሚል ርዕስ በደራሲ ክሌይቦርን ካርሰን ለንባብ የበቃው መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፣ ማርቲን ሉተር የተወለደው  ጥር 15, 1929 በደቡባዊ አሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ውስጥ ነበር፡፡ ከአንድ የሃይማኖት አባትና አስተማሪ እናት ነው ኪንግ የተወለደው። አባቱ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ (ፓስተር) የነበሩት ኪንግ፣ የአባቱን ፈለግ በመከተል  እሱም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ  ፓስተር ሆኖ አገልግሏል።

ኪንግ በጆርጂያ ውስጥ  ለጥቁሮች ብቻ በተፈቀደው የሕዝብ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር  እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሥራ አምስት ዓመቱ ያጠናቀቀው ማርቲን ሉተር፣ በ1948  አባቱ እና አያቱ ከተመረቁበት ሞርሃውስ ኮሌጅ ከአትላንታ ታዋቂ የጥቁር ማህበረሰብ ተቋም የመጀመሪያ (B.A.) ዲግሪ በሶሲዮሎጂ አግኝቷል። በፔንስልቬንያ ውስጥ ከሚገኘው በክሮዘር ቲዎሎጂካል ሴሚናሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል የነገረ መለኮት (Theology) ትምህርቱን አጠናቅቋል፡፡ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በ1953  ካጠናቀቀ በኋላ በ1955  የዶክትሬት ዲግሪውን (ፒ ኤች ዲ) በማጠናቀቅ በክብር ተመርቋል፡፡ 

ከትምህርቱ ጎን ለጎን በ1954፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሞንትጎመሪ፣ ኦላባማ የዴክስተር አቬኑ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ጊዜ ምዕመናንን ሃይማኖታዊ ትምህርትን ከማስተማር ጎን ለጎን፤ አሜሪካ ውስጥ ለሚኖሩት የጥቁር ማህበረሰብ ሰብዓዊ መብታቸው በህግ እንዲታወቅና እንዲጠበቅ ብርቱ ትግል ማድረግ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ በዓይነቱ ግንባር ቀደም ድርጅት የሆነውና ለጥቁሮች መብት የሚከራከር ማህበር  (National Association for the Advancement of Colored People) በመመስረት የማህበሩ ሊቀ መንበር በመሆን የነጻነት ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ችሏል፡፡ 

በታህሳስ 1955 መጀመሪያ ላይ ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያውን ታላቅ የጥቁር ህዝቦች ሰላማዊ ሰልፍ በማስተባበርና በመምራት ኪንግ ግንባር ቀደም ሚና መወጣት ቻለ። ይህ የተቃውሞ ሰልፍ አውቶብስ ውስጥ ነጮች ከፊት ጥቁሮች ከኋላ እንዲቀመጡ የሚያዝዘውን ህግ በመቃወም አውቶብሶችን ያለመጠቀም አድማ አስጀመረ፡፡ ደራሲ ክሌይቦርን ካርሰን ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ እንዳሰፈረው፤ ይህ አድማ ለ382 ቀናት ዘልቋል። በዚህ አድማ ጫና ምክንያት በታህሳስ 21 ቀን 1956 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአውቶቡሶች (የህዝብ ትራንስፖርት) ላይ የሚደረገውን መድልዖ እንዲቀር ካወጀ በኋላ በእኩልነት መሳፈር ጀመሩ። ነገር ግን በእነዚህ የአድማ ጊዜያት ውስጥ ማርቲን ሉተር ኪንግ  በፖሊሶች ተይዟል፡፡ ቤቱ  በቦምብ ተደብድቧል፡፡ ግላዊ ጥቃትም ደርሶበታል፡፡ ፈተናዎች ያልበገሩት ይህ ሰው ግን የጥቁሮች መብት ሙሉ በሙሉ ዋስትና እስኪያገኝ ድረስ ትግሉን መቀጠሉን ክሌይቦርን ካርሰን በኪንግ ግለ-ታሪክ ውስጥ አስፍሯል፡፡

ቶማስ ጃክሰን ‘From Civil Rights to Human Rights: Martin Luther King Jr. and the Struggle for Economic Justice’ በሚል ርዕስ በ2006 ለንባብ በበቃው መጽሐፉ፣ በነሐሴ 1963 ማርቲን ሉተር ኪንግ በዋሺንግተን ያደረገው “ህልም አለኝ” ንግግር በሲቪክ መብቶች እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ይላል። በወቅቱ  ከአመጽ ነጻ በሆነ መልኩ እንዴት ለውጥን ማምጣት እንደሚቻልና የዘር እኩልነትን ማስፈን እንደሚገባ መርሁን በግልጽ ማስቀመጡንም ያትታል።

በቀጣዩ ዓመት (1964) በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ጥቁሮች እንዲያልፉ ወይም በሁሉም ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዲሠሩ የሚፈቅደው ሕግ ጸደቀ። ነገር ግን የመብት ጥያቄው ገና በጅምር በሚባል ደረጃ ላይ ነበር። እኩልነትን የማይቀበሉ ነጮች በወቅቱ ዘረኛ ፖሊሲዎች እንዲወጡ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩ ነበር። በደቡባዊ ግዛቶችም ጥቁሮች በተለይ ምርጫ ላይ ያላቸውን ተሳተፎ በእጅጉ የሚቀንሱ ፖሊሲዎች ይወጡ እንደነበር በደራሲ ክሌይቦርን ካርሰን የተጻፈው መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡ 

ማርቲን ሉተር 1965 ላይ መሰል ሕጎች እንዳይወጡ የሚቃወመውን በአለባማ ሞንቶጎመሪ  የተቃውሞ ሰልፍ አካሂዷል። በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ከነጭ የፀጥታ ሃይሎች የጠበቃቸው ጭካኔ የተሞላበት ምላሽ ነበር። ነገር ግን  በጥር 1965  ማርቲን ሉተር ከፕሌይ ቦይ መጽሔት አዘጋጅ ከአሌክስ ሃሌይ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ኩነቱን አስመልክቶ በሰጠው ቃል፣ “አሁንም ከአመጽ የጸዳ በሚለው መርሃችን በመመራት የመብት እንቅስቃሴያችንን እንቀጥላለን” ሲል ሰላማዊ ትግል የመጀመሪያና የመጨረሻ መርሁ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ይህን ተከትሎ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚደረጉ ኃይል ያልተቀላቀለባቸው የመብት ጥያቄዎችና የነጻነት ትግሎች (Nonviolence struggle) ከማህተመ ጋንዲ ቀጥሎ ከሚጠቀሱ ባለ ታሪከኞች መካከል ማርቲን ሉተር ኪንግ አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ማርቲን ሉተር ለአፍሪካ-አሜሪካውያን ያደረገው የነጻነት ትግል ጥረት እና መስዋዕትነት በዓለም ታሪክ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ ያደርገዋል፡፡ ከምንም በላይ ለአፍሪካ አሜሪካውያን የኪንግ የህይወት መንገድ እንደተምሳሌትነት የሚወሰድ ነው፡፡

የክፍለ-ዘመኑ ተምሳሌታዊ ጀግና የሆነው የማርቲን ሉተር ህልፈት ግን አሳዛኝ ነበር፡፡ ሐሙስ ሚያዝያ 1968  አስደንጋጭ የሆነ አንዳች ድንገተኛ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ማርቲን ሉተር በሜምፊስ ለሰልፈኞች ንግግር በሚያደርግበት ወቅት፣ አልሞ ተኳሽ በሆኑ ነፍሰ ገዳዮች በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱን ተነጠቀ፡፡

በአጠቃላይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ከአመጽ የጸዳችና በመግባባት ላይ የተመሠረተች አሜሪካን ያስብ ነበር። ዘረኝነት የተወገደባት፣ እኩልነት የሰፈነባት ሀገረ አሜሪካን ማየት ትልቁ ሕልሙ ነበር፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ በሀገረ-አሜሪካ ውስጥ በአፍሪካ አሜሪካውያን የእኩልነት ጥያቄ ውስጥ የማርቲን ሉተር ህልም ሙሉ ለሙሉ ዕውን መሆን ባይችልም ከፍተኛ ውጤት ግን አስገኝቷል፡፡ ከምንም በላይ ግን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፤ ከጭካኔ ይልቅ ርህራሄን፤ ሃይል ከቀላቀለ ዓመጽ ይልቅ ሰላማዊ ትግልን በተግባር በማሳየት ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review