ማዕከላቱ ከዓላማቸው አንጻር ሲመዘኑ

You are currently viewing ማዕከላቱ ከዓላማቸው አንጻር ሲመዘኑ

“ወጣት የነብር ጣት” ይባላል በተለምዶ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ነብር ራሱን ለመከላከልም ሆነ አድኖ ለመብላት ከሚጠቀምባቸው የሰውነት ክፍሎች ዋነኛው ጣቱ ነው፡፡ ወጣትም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አይተኬ ሚና የሚጫወት ሃይል እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ጋር እንዲዛመድ ተደርጎል፡፡

ይህ የህብረተሰብ ክፍል ሚናው አውንታዊ እንዲሆን ካስፈለገ ሰብዕናውን ሊገነቡ፣ ጊዜውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፍ የሚያደርጉ ስራዎች መሰራት አለበት፡፡ አዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት የመገንባቷ ምክንያትም ከዚህ መነሻነት መሆኑን መናገር “ለቀባሪ ማርዳት” ነው የሚሆነው። ማዕከላቱ ምን ያህል ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ ነው? የሚለው ግን ሊነሳ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ወቅቱ ከበጋው በተሻለ ወጣቱ የመዝናኛ ጊዜ የሚያገኝበት መሆኑ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ማዕከላት እንድንቃኝ ወጣቶችም በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩን ወደድን፡፡ 

ወጣት አቤል መስፍን ይባላል፡፡ በተለምዶ ሳንሱሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል። እንደ ወጣቱ ገለጻ፣ ባለው የእረፍት ጊዜ ወደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል በማቅናት የጅምናዚየም እንዲሁም የፑል ጨዋታ አገልግሎት ይጠቀማል፡፡ ከዚህ ቀደም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ባለመኖሩ ምክንያት ጊዜውን በአልባሌ ቦታዎች ያሳልፍ ነበር፡፡ በተለይም የስራ እረፍት በሚኖረው ሰዓት ጊዜ ለማሳለፍ በሚል ለሱስ ተጋላጭ በሚያደርጉ ተግባራት ተጠምዶ እንዳሳለፈ፣ “የት መሄድ እንዳለብኝ፣ ከማን ጋር የእረፍት ጊዜ ማሳለፍ እንደሚገባኝ ባለማወቄ ምክንያት ጫት በመቃም እንዲሁም ሲጋራ በማጨስ ጊዜዬን አሳልፍ ነበር። ዘግይቼም ቢሆን እየሄድኩበት ያለው መንገድ እንደማያዋጣኝ በመረዳት ወዲያው ውሳኔ በመወሰን ከሱስ ነፃ ለመሆን ችያለሁ፡፡” ሲል አብራርቷል፡፡

ከሱስ እና ከአልባሌ ተግባራት መራቅ ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነ የሚናገረው ወጣት አቤል፤ ጤናማ ብሎም ማህበራዊ መስተጋብሮቻችንን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያምናል፡፡ ይህንንም ወደ ተግባር በመለወጥ በወጣት ማዕከል የጅምናዚየም ስፖርት በቋሚነት ይሰራል፡፡ በዚህም በጤናው፣ በአካል እና በመንፈስ ጥንካሬው ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ እንዳገዘው ከልምዱ ይመሰክራል፡፡ “ፑል ለመጫወት ስመጣ ከማገኛቸው ወጣቶች ጋር ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ችያለሁም” ብሏል፡፡

ከሱስ እንዲወጣ፣ በአካል እና በመንፈስ እንዲጠነክር፣ ማህበራዊ መስተጋብሩን እንዲያሻሽል ትልቅ እገዛ ያደረገለት ማዕከሉ፤ ለእርሱ እና ለመሰል ወጣቶች የሚሰጠውን አገልግሎት በተሟላ መልኩ እንዳይሰጥ የተለያዩ ችግሮች አንቀው እንደያዙት ወጣት አቤል አልሸሸገም። እንደ እርሱ ገለፃ ከሆነ፤ የመብራት መቆራረጥ እንዲሁም የሻወር አገልግሎት በሚፈለገው ልክ አለመኖር ወደ ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል የመምጣት ልምዱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀንስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ መብራት ለረጅም ሰዓታት ይጠፋል። እንደ ኤሮቢክስ ያሉ ስፖርቶችን ለመስራት መብራት አስፈላጊ ነው፡፡ ክፍሎቹም ሲጨልሙ ለመስራት ያለን ፍላጎት ይጠፋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በማዕከሉ የኳስ ሜዳ ቢኖር ለወጣቶች ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ ይፈጥርላቸዋል ሲል ቢታይ ያላቸውን ነገሮች አብራርቷል፡፡

ወጣት እመቤት የሺጥላም የወረዳው ነዋሪ ናት፡፡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደ ወረዳው የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል በማቅናት መጽሐፍትን እንደምታነብ ገልጻልናለች፡፡ ሆኖም ቤተ መጻሕፍቱ ሁልጊዜ ክፍት አለመሆኑ፣  የማንበቢያ ክፍሉ ለማንበብ የማይመችና የማይጋብዝ መሆኑ፣ በመጽሐፍት መልክ (ሀርድ ኮፒ) ተዘጋጅተው የማይገኙ አንዳንድ መጽሐፍትን ከተለያዩ ገጸ ድሮች ለማንበብ የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት  በቤተ መጻሕፍቱ አለመኖሩና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫዋ እንደማታደርገው ገልጻልናለች፡፡ በቀጣይ ቤተ መጻሕፍቱ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ፣ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሻሻል መጪውን የክረምት ጊዜ እውቀታችንን የምናሳድግበትና ጥሩ የትምህርት ዝግጅት የምናደርግበት እንዲሆን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትኩረት ይስጡት ስትልም አጽንዖት ሰጥታ ተናግራለች፡፡

ለብዙ ወጣቶች ሰብዕና መገንቢያነት እንዲውል ተደርጎ በተገነባው ማዕከል ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማረም እና በተጠቃሚዎች ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ምን እየሠራ እንደሆነ ጠይቀናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሻቸውን ያጋሩን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል የወጣቶች አቅም ማጎልበት ቡድን መሪ ወይዘሮ በላይነሽ ተሰማ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በወጣት ማዕከሉ የተለያዩ ስፖርታዊ የመዝናኛ ጨዋታዎች፣ የአዳራሽ አገልግሎት፣ የካፍቴሪያ አገልግሎት፣ የጂምናዚየም እና መሰል አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛል፡፡ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራትም  6 ሺህ 50 የሚሆኑ ወጣቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ማዕከሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ ያሉ ውስንነቶችን ወ/ሮ በላይነሽ ሲያብራሩ፣ “አንዳንድ ጊዜ ወቅታዊ ጉዳዮች ሲገጥሙ የወረዳ አመራሮች በራሳቸው ፍቃድ የስብሰባ አዳራሹን የመጠቀም ነገር አለ፡፡ በተቻለ መጠን የቤተ መጻሕፉቱን የማንበቢያ ክፍልን ሳቢ በሆነ አግባብ በማደራጀት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሰራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡

አክለውም፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት በመሰረታዊ የኮምፒዩተር ስልጠና በተደራጀ አግባብ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ እና የሲስተም ችግር ነው። ለመፍትሔውም ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ያሉ የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት እየሰጡ ስላለው አገልግሎት ለመመልከት ሌላኛው ቅኝት ያደረግንበት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቁጥር 2 የወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ነው፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ወጣት ቃለአብ ገረመውን፤ በዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሲያነብ አግኝተን በሰጠን አስተያየት፤ “ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ቤተ መጻሕፍት ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር፡፡ አሁን ግን በመኖሪያ አካባቢዬ ይህን መሰሉ አገልግሎት መሰጠቱ ትልቅ እፎይታን ፈጥሮልኛል፡፡ በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት ስላለ የምፈልገውን ነገር በማውረድ እንዳነብ አድርጎኛል፡፡ የተለያዩ መጽሐፍትም ስላሉ የንባብ ክህሎቴን አዳብሮልኛል፡፡ የኮምፒዩተር እውቀቴንም አሻሽሎልኛል። ብዙ ጊዜ የማነብበው ፈተና ሲቃረብ ነበር፤ አሁን ግን በወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት የምፈልገውን አገልግሎት ማግኘት ችያለሁ” ብሏል፡፡ 

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰግድ ተሾመ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ሞዴል ለመሆን የቻለ ነው። ቁጥራቸው 18 የሚሆኑ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ከእነዚህም መካከል ስፖርታዊ የመዝናኛ ጨዋታዎች፣ ወጣት ተኮር የጤና አገልግሎት፣ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ የካፍቴሪያ፣ የጤናና የሥነ ተዋልዶ፣ የሻወር፣ የሴቶች የውበት ሳሎን፣ የወንዶች የውበት ሳሎን፣ ጌም ዞን፣ ሳይንስና ፈጠራ፣ የዲ ኤስ ቲቪ፣ የጂምናዚየም፣ የክብደት ማንሳት አገልግሎት፣ እንደ ከረምቡላና ፑል ያሉ የቤት ውስጥ ጨዋታዎች፣ የተለያዩ ክበባት በስፖርት ሰርከስ እና ቴኳንዶ፣ በአርት ዘርፉ ውዝዋዜ ዳንስ እንዲሁም በቴአትርና  በመሳሰሉት  አገልግሎት  እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት 52 ሺህ 254 ወጣቶችን ተዳራሽ ያደረገ አገልግሎት መስጠቱን የሚናገሩት የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ፣ በክረምቱ መርሐ ግብር 25 ሺህ ወጣቶችን በተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ስለመታሰቡ ጠቁመዋል፡፡  በበጎ ፈቃደኛ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የትምህርት ስልጠና የመስጠት፣ ከጤና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በወር አንድ ጊዜ ለሁሉም ማህበረሰብ የጤና ምርመራ የማድረግ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሳታፊ መሆን እንዲሁም የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ የሰው ሃይል እጥረት እንዳለበት በመጠቆምም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ሁሉም ሰራተኛ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በመስራቱ ውጤታማ ለመሆን መብቃተቸውን አብራርተዋል፡፡

በከተማችን ያሉ የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ሁለት መልክ ያላቸው እንደሆኑ ከላይ ያነሳናቸው ማዕከላት አስረጅዎች ናቸው፡፡ ይህን ከግምት ያስገባ ስራም ከሚመለከተው የመንግስት አካል ይጠበቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል አገልግሎት ልማት ቡድን መሪ አቶ ሳሙኤል ምትኩ፤ በከተማ አቀፍ ደረጃ ያለውን የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ያሉበትን ሁኔታ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃቸውን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ማዕከላቱ ወጣቶች ከተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተላቅቀው በከተማዋ ልማት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ራሳቸውን ለማዝናናትና በእውቀት ለመገንባት እንዲችሉ የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ  ማዕከላቱ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ 

እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሚያስተዳድራቸው 114 የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት አሉ፡፡ የሚሰጡት አገልግሎት በአራት ይከፈላል፡፡ ሞዴል፣ ሁለገብ፣ መለስተኛ እና አነስተኛ ተብለው ይከፈላሉ። ሞዴል የሚባሉት ከአስራ ስድስት በላይ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ 33 ማዕከላት ናቸው፡፡ ሁለገብ የሚባለው ደረጃ ደግሞ ከአስራ ሦስት በላይ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የማዕከላቱ ቁጥርም 47 ናቸው፡፡ መለስተኛ በሚባል ደረጃ የሚገኙት ከዘጠኝ በላይ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ ቁጥራቸውም 24 ነው። አነስተኛ የሚባሉት ደግሞ ከአምስት በታች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ቁጥራቸውም 10 ነው፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ ቢሮው አነስተኛዎችን ወደ መለስተኛ፣ መለስተኛዎችን ወደ ሁለገብ እንዲሁም ደግሞ ሁለገቦችን ወደ ሞዴልነት እንዲመጡ ማስቻል ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የመገልገያ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ ተሰርቷል፡፡ ከመብራት ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ ሳሙኤል በሰጡት ምላሽ ማዕከላቱ አቅማቸው ደከም ብሎ መክፈል ሲቸገሩ እንዲሁም በተለያዩ ልማቶች ምክንያት የመብራት መቆራረጥ ይገጥማል፡፡ እርሱም እንዲፈታ ባለን ትስስር መሰረት ከመብራት አገልግሎት ጋር በመነጋገር ችግሮች እንዲፈቱ የማድረጉን ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ጉዳዩም በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

የባለሙያ እጥረት ባለባቸው የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ጉድለቶችን ለመሙላት የመፍትሔ ሃሳብ አቅርበዋል። በዚህም መሰረት  እንደ ከተማ የባለሙያ ቅጥር ቆሟል፡፡ መፍትሔ የሚሆነው ያሉ ባለሙያዎችን በውክልና እንዲሰሩ ማድረግ በመሆኑ ያንን ማድረግ ተችሏል። ከዚያ በተጨማሪ የክረምት ብሎም የበጋ ቋሚ በጎ ፍቃደኞች አሉ፡፡ የቤተ መጻሕፍት ቤቱ ባለሙያ ባይኖር እንኳ በበጎ ፍቃደኛ እንዲሸፈን የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ ሌላው ደግሞ ስብሰባዎች ሲኖሩ የአዳራሽ መጨናነቆች ይፈጠራሉ። ክበባት ላይ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች የመስሪያ ፕሮግራማቸውን በማይጋፋ መልኩ እንዲካሄድ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በተቀመጠው ፕሮግራም መሰረትም የሚገለገሉ አካላት እራሳቸው ስብሰባውን እንዲያስተባብሩ እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

በ9 ወር ውስጥ በድግግሞሽ 4 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ውስጥ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ በመጪው ክረምት በእቅድ ደረጃ ቢሮው ሊሰራቸው ያሰባቸው ተግባራት ሰብዓዊ አገልግሎት፣ አረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ አገልግሎት፣ ትምህርትና ስልጠና አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎት እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ፌስቲቫል በማድረግ በማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ ይገኙበታል፡፡ በዚህም 334 ሺህ 293 በላይ ወጣቶችን ያሳተፈ ብሎም 257ሺህ 426 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

የወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ወጣቶች በአካልና በአዕምሮ እንዲዳብሩ ብሎም የተሟላ ሰብዕና እንዲኖራቸውና አልባሌ ቦታዎች ላይ ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉ የሚያግዝ በመሆኑ የከተማዋን ወጣት በሚመጥን መልኩ ለማሻሻል ዘመኑን በዋጀው የሶፍት ኮፒ አገልግሎት ወጣቶቹ በስልካቸውም ሆነ በኮምፒዩተር አውርደው እንዲጠቀሙ ነፃ የዋይፋይና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙና  ወደ ሳይንስ ካፌ እንዲያድጉ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review