ምክር ቤቱ በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ይሰራል -አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

You are currently viewing ምክር ቤቱ በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ይሰራል -አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

AMN-የካቲት 19/2017 ዓ.ም

የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ /ፕሮፋይል ጥናት ፕሮጀክት ላይ በአጋርነት ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ስምምነቱን ያፈራረሙት የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነቶች ተጠንተው ተግባራዊ መደረጋቸው የኢትዮጵያን ኅብረብሔራዊ አንድነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ለማጽናት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአገር ባለቤትነት መብታቸው እንዲከበርና በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለብዙ ዘመናት በአንድነት ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች እንደሆኑ ያመላከቱት አፈ ጉባኤው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እነማን ናቸው? በየት አካባቢ ይኖራሉ? ብዛታቸው፣ ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥናት መመለስና ለትውልድ ማስተላለፍ ሕዝቦች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በትክክል በማወቅ የሚገባቸውን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ፣ ማንነታቸው መገለጫ የሆኑትን ነባር ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮችና እምነቶች እንዲጠኑና ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል አበርክቶው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ መልካዓ ምድራዊ አሰፋፈራቸው፣ የስነ ልቦና አንድነታቸው እንዲጠኑላቸውና እንዲበለጽጉላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አስታውሰው ዛሬ የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት በጥበብና በጥብቅ ዲስፕሊን በመምራት ለሕዝቦች ጥያቄ መላሽ መስጠት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የፌደሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review