ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው- ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

You are currently viewing ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው- ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

AMN-ሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“የመሀሉ ዘመን” በሚል ርዕስ ትንታኔ ያቀረቡት ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች ሳንዘናጋ ለበለጠ ድል መትጋት ይገባል ብለዋል።

ታላቁን የህዳሴ ግድብ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ገንብተን በማጠናቀቅ ሀገርና ህዝብን አንገት ከማስደፋት ለማዳን የተቻለበትና የጠላቶቻችን የተቀናጀ ሴራ ያከሸፍንበት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ኢኮኖሚውም ፈተናዎችን በመቋቋም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መረጃዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል።

ባለፉት ዓመታት ብዙ ሀገራት በዲፕሎማሲው መስክ በትብብር ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውንና ይህንን በጎ ዕድል በመጠቀም የብሄራዊ ጥቅምን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥና የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን የቀረበው ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍትሃዊ አጀንዳ ሆኖ መያዙንም መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሠላምን ለማፅናትና ብልፅግናንን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትም ባስመዘገባቸው ድሎች ሳይኩራራ ለበለጠ ተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል ብለዋል።

በውይይቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review