•በበጀት ዓመቱ እስካሁን ለ324 ሺህ 282 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ እንደንስር እራሷን እያደሰች ትገኛለች፡፡ ከሕንፃዎቿ ውበት ከፍ ባለው የነዋሪዎቿ ፈገግታ ይበልጥ እየደመቀች የመጣችው ይቺ ከተማ በሰው ተኮር ፕሮጀክቶቿ የበርካቶችን እንባ እያበሰች ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የመዲናዋ ነዋሪዎች ምስክር ናቸው፡፡
በመዲናዋ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት እየተከናወኑ ከሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የሰው ተኮር ፕሮጀክት ስራ አንዱ ነው። ፕሮጀክቱም ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የሸገር ዳቦና የአትክልት መሸጫ ሱቆች፣ የምገባ ማዕከላት፣ የከብት እና የዶሮ እርባታ ሼዶች፣ የአደባባይ ማስዋብ ስራ፣ የልጆች መጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን እንዲሁም በትምህርት ቤት የሚከናወኑ ምገባዎችን ጨምሮ ሌሎች ሰው ተኮር ስራዎች ማህበራዊ ፍትህን ማንገሻ፣ የዜጎችን እንባ ማበሻ እና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትም ጋሻ ናቸው፡፡
“ማን ይናገር የነበረ…አሊያም ከፈረሱ አፍ” እንዲሉ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጉለሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ከሆኑ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በወተት ልማት የተሰማሩ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው በተመቻቸላቸው የስራ ዕድል ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡
ከተጠቃሚዎቹ መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሚገኙት ፋሲካ አየለ እና ጓደኞቻቸው የወተት ከብት እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ቸርነት አየለ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚለው እሱና መሰሎቹ በወተት ልማት ዘርፍ መሰማራታቸው ውጤታማና ትርፋማ እንዳደረጋቸው ተናግሯል፡፡
አምስት ወጣቶች ሆነው የተደራጁት እነ ወጣት ቸርነት፣ የሥራ ዘርፉ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰባቸውና ለሌሎችም ጥቅም እያስገኘ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ መንግስት ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታ ሼድ በመጠቀም በወተት ልማት ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁሞ ወጣቶች አልባሌ ቦታ በመዋል ጊዜያቸውን ከማባከን ይልቅ ስራ ሳያማርጡ በመስራት ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን መጥቀም እንደሚገባቸውም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ የሰው ተኮር ፕሮጀክት ወጣቶችና ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ በማድረግ ለበርካቶች የስራ እድል እየፈተረ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ወጣት ቸርነት ገልጿል፡፡
ወይዘሪት አስናቁ ካሳዬ በሰው ተኮር ፕሮጀክት በወረዳው የመስሪያ ቦታ ሼድ ከጓደኞቿ ጋር ተሰጥቷቸው አምስት ሆነው ተደራጅተው በብሎኬት ማምረት ዘርፍ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሪት አስናቁ በሰው ተኮር ፕሮጀክት ቋሚ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጻ፣ ፕሮጀክቱም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ታስረዳለች፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 “የእንስራ” ሸክላ ስራ አባል የሆኑት ወ/ሮ እመቤት ከበደ በክፍለ ከተማው የሸክላ ስራ መስሪያ ቦታ ሼድ መሰራቱ የትም አካባቢ ተበታትነው ይሰሩ የነበሩ ሸክላ ሰሪ እናቶች በአንድ የመስሪያ ቦታ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አበበች አለሙ በሰው ተኮር ፕሮጀክት በተሰራ የምገባ ማእከል ውስጥ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው፡፡ እንጦጦ አካባቢ ብዙ እናቶች እንጨት በጀርባቸው አዝለው በመሸጥ ሕይወታቸውን ይገፉ ነበር፤ መንግስት ለእነዚህ እናቶች በከተማ ግብርና እና በእንጀራ መጋገር የስራ ዘርፍ አደራጅቶ ተጠቃሚ ማድረጉ እንዳስደሰታቸው ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል። ይህን መሰል ስራ እንዲህ ለእናቶች ትልቅ እፎይታን ያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ መኩሪያ ጉርሙ በክፍለ ከተማው የተገነቡ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የዜጎችን ችግር በመፍታት በስራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ክፍለ ከተማው በኑሮ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩበት ክፍለ ከተማ መሆኑን አቶ መኩሪያ አንስተው ምክር ቤቱም በየጊዜው በችግር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ላይ ውይይት እና ክትትል ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ነዋሪዎች በክፍለ ከተማው ሲያነሷቸው የነበሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመው የሜጋ ፕሮጀክቶችን እና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በመስራት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በእንጦጦ አካባቢ እንጨት በመልቀም እና ቅጠል በመሰብሰብ ይተዳደሩ የነበሩ እናቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የእንጀራ ፋብሪካ በመገንባት ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚያቸውን ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውንም ገልፀዋል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የስራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ ገብረሚካኤል እየተገነቡ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች የስራ እድሎችን በመፈጠር የዜጎችን ችግር የፈቱ እና ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መለሰ ገለጻ በአብዛኛው የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት የስራ እድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡ በንግድ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና በዶሮ እርባታ እና በወተት ልማት፣ በማድለብ እንዲሁም በአገልግሎት የስራ እድል የተፈጠረባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በክፍለ ከተማው በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የስራ እድል ፈጠራው በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን አቶ መለሰ ገልጸው በበጀት ዓመቱ አስር ወራት እስካሁን ለ32 ሺህ 959 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 25 ሺህ 708 ወጣቶች ሲሆኑ 14 ሺህ 172 ሴቶች ደግሞ በስራ እድሉ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
በወጣቶች ላይ የነበረውን የስራ ማማረጥ ችግሮችን በሂደት ቀስ በቀስ በመፍታት ስራን ሳያማርጡ ያገኙትን ሰርተው እንዲለወጡ እያደረጉ ሲሆን የሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ መለሰ ገልጸዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይከበር ስማቸው የሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በማጠናከር የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወጣቶችና ሴቶችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ይከበር በክፍለ ከተማው ዘላቂ የሆኑ የስራ እድል መፍጠሪያ ሼዶች ላይ ወጣቶች ገብተው ራሳቸውን እንዲያበለጽጉ፣ ሀገርን፣ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲጠቅሙ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ በስራና ክህሎት ቢሮ የስራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ችግር እየፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የሚሰሩት የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የስራ ዕድል ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመው በዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
ከፕሮጀክቶች፣ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከንግድ እና አገልግሎት ዘርፎች የስራ እድሎችን በመለየት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት (ይህ መረጃ እስከተሰበሰበበት ድረስ ብቻ) ለ324 ሺህ 282 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ለዜጎች 62 በመቶ በቅጥር እና 38 በመቶ ደግሞ በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመት (ይህ መረጃ እስከተሰበሰበበት ድረስ ብቻ) 13 ሺህ 15 የሚሆኑ ዜጎችን በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት መቻላቸውን አቶ ሰብሀዲን ገልጸዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ትልቁ የመንግስት ፕሮጀክት ሲሆን በ1ኛው እና በ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት 100 ሺህ 180 የሚሆኑ ዜጎች በቋሚ እና ጊዜዊነት የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በሚፈጠሩ የስራ ዕድሎችም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ እስካሁን የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡
በንግድ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና በዶሮ እርባታ እና በወተት ልማት፣ በማድለብ እንዲሁም በአገልግሎት የስራ እድል የተፈጠረባቸው ዘርፎች መሆናቸውን አቶ ሰብሀዲን ጠቁመዋል፡፡
በይግለጡ ጓዴ