ሲቪል ማህበራት ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የጀመሩትን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ፡፡
ምክትል ከንቲባዉ አቶ ጃንጥራር አባይ ከአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ማህበራት ተወካዮች ጋር በወቅታዊ፣ ከተማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ዓለም አቀፍ አንድምታ ያለውን የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ፤ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የገበያ ሰንሰለቶችን ለማሳጠር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በተማሪዎች ምገባ አገልግሎት ፣ የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በመዘርጋት ፣ በትራንስፖርት እና በጤናው ዘርፍ በሚደረጉ ድጎማዎች ፣ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም እና በመሳሰሉት ዘላቂ መፍትሄ ላይ ያተኮሩ ርብርቦች እየተደረጉ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።
በርካታ ችግሮች ወደ ድል እየተቀየሩ ከተማዋና ሀገሪቷ በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል ከንቲባዉ በዚህ ሂደት ዉስጥ የሲቪክ ማህበራት ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ሲቪል ማህበራት የጀመሩትን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ኋላቀር የፖለቲካ ባህል እንዲዘምን እና የዲሞክራሲ ባህል ግንባጻ እንዲፋጠን ከማድረግ ረገድ የሲቪክ ማህበራት ያላቸዉ ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጡን ከሌብነት እና ከብልሹ አሰራሮች ነፃ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ሁሉንም ያማከለ አሳታፊና ፍትሀዊ ልማት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኢትዮጵያን ለማሻገርና የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል እያደረጉ ያሉትን ጥረት እንደሚደግፉም አመላክተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ