ሴት ተማሪዎችን ከጥቃት መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት

You are currently viewing ሴት ተማሪዎችን ከጥቃት መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት

ይህን ፅሁፍ ለመከተብ የተገደድኩት ሴት ስለሆንኩ፣ ከሴት በመወለዴ ወይም የሴቶች ልጆች እናት ስለሆንኩ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በተለይ በአዲስ አበባ ደረጃ ውጤታማና ጠንካራ አዳጊ ሴቶች በየትምህርት ቤቱ እየወጡና የነገ ሀገር ተረካቢነታቸው እያበበ በመምጣቱ ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ በማሰብ ጭምር ነው።

በሴቶች ላይ ጫና የሚያሳድሩ አሉታዊ ድርጊቶች፣ ፆታዊ ጥቃቶችና መሰል ጥፋቶች አሁንም ድረስ አለመቀረፋቸው ጉዳዩን ደጋግመን እንድናነሳው ያስገድደናል ብዬ ስለማምን ነገሩን በአንድ ገጠመኝ ለመጀመር ወደድኩ። በቅርቡ ከቢሮ ውጪ የሚሰራ ስራ አጋጠመኝና በከተማችን ወደሚገኝ አንድ አካባቢ ሄጄ ነበር፡፡ የቀጠሮዬ ሰዓቴ እስከሚደርስም በአቅራቢያው ወደ ተመለከትኩት አንድ ሆቴል ጎራ አልኩኝ፤ የምፈልገውን አዝዤ ጥግ ላይ ተቀምጬ አላፊ አግዳሚውን መቃኘት ጀመርኩ፡፡ ይሄኔ ነበር ለመገመት እንኳን የሚያዳግት ነገር የተመለከትኩት፡፡

አንድ ዕድሜው ወደ ጎልማሳነት የተጠጋ ሰው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሰችን ሴት ተማሪ ይዞ ወደ ግቢው ገባ። እኔም ዝም ብዬ ስታዘብ በተቀመጡበት ወንበር ምግብና ለስላሳ መጠጥ ተጠቅመው ሊወጡ ነው ስል ቆይተው አልጋ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ያኔ ታድያ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ ልጅቷን ጠርቼ በቁጣ ማነጋገር ጀመርኩ።

“እንዴት መጣሽ? የት እንዳለሽ ታውቂያለሽ? ዮኒፎርም ለብሶ ያውም በአንቺ እድሜ እንዲህ ያለ ቦታ መገኘት ተገቢ ነው?” እያልኩ በጥያቄ ሳጣድፋት እምባዋ ቀደማት። ወደቀልቧ ለመመለስ እየሞከረች፣ “ወንድሜ ነው፣ ትምህርት ቤት አርፍጄ አትገቢም ተብዬ ነው፣ ከሌሎች አርፋጅ ተማሪዎች ጋር ቆመን አግኝቶኝ ለስላሳ ልጋብዝሽ ብሎኝ ነው የመጣሁት” አለችኝ፡፡ እርሷ ይህን ትበል እንጂ ምንም አይነት ስጋዊ ዝምድና እንደሌላቸው ሁኔታቸውንም መልካቸውንም አይቶ መገመት አያስቸግርም ነበር፡፡

በዚህ መሃል ታድያ እንደምንም አግባብቼ መታወቂያዋን እንድታሳየኝ ጠየኳት፡፡ ከመታወቂያዋ መረዳት እንደቻልኩትም ይህቺ አዳጊ ኮተቤ አካባቢ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ መሆኗን ነው፡፡ መታወቂያዋን ፎቶ ግራፍ ሳነሳም ‘ምን አገባኝ’ ብዬ በቀላሉ እንደማልተዋት ስለተረዳች እግሬ ላይ ወድቃ፣ “ይቅርታ አድርጊልኝ፤ ሁለተኛ አይለመደኝም፤ ቤተሰቦቼ እንዳይሰሙብኝ” እያለች ተርበተበተች። የምታደርገው ነገር ትክክል አለመሆኑንና ለከፋ የህይወት ጉዳት ሊዳርጋት እንደሚችል፣ በቀጣይ ትምህርት ቤቷ ድረስ ሄጄ እንደምከታተላት አስጠንቅቄ ይዟት ከመጣው ሰውም ነጥዬ ወደ ቤቷ ላክዃት፡፡

ተማሪዋ ፈጥና ከሆቴሉ ብትወጣም እኔ ግን ነገሩን ለረጅም ደቂቃ ማብሰልሰል ጀመርኩ፡፡ ወላጆች ልጆቻችን የትና እንዴት? እንደሚውሉ እናውቃለን ወይ? መምህራንስ ቢሆኑ ምን ያህል ተማሪዎቻቸውን ይከታተላሉ? ስል አብዝቼ አሰብኩ።

እንደዚህች ተማሪ ሁሉ በከተማዋ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎች ለደቂቃ አረፈዱ ተብሎ ከትምህርት ቤት ግቢ የማስወጣት ነገር በተደጋጋሚ እመለከታለሁ። ይህም ልጃአገረዶችንና ወጣት ወንዶችን ከቤትም ከትምህርትም ሳይሆኑ በአልባሌ ቦታ እንዲውሉ ያደርጋል። ለመጥፎና አጓጉል ድርጊትም ያጋልጣል።

በእርግጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተገበራቸው ጥብቅ እርምጃዎች፣ በብዙዎቹ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ያሉ የመጠጥ፣ ጫትና መሰል አዋኪ ነገሮች መሸጥ እየቀነሰ ነው። ያም ሆኖ ሴት ተማሪዎች በቀላሉ እየተታለሉ ለጥፋት እንዳይጋለጡ ወላጅና ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ መላው ማህበረሰብ መትጋት አለበት።

በየትኛውም ስፍራና ሁኔታ በሴቶች ላይ ማንኛውም አይነት ጥቃት ፈፅሞ እንዳይፈፀም ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ትውልድ ላይ እየታየ ያለውን የሴቶች ውጤታማነት አጠናክሮ  ለመቀጠል እገዛው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ሴት ተማሪዎችን በማታለል ወደ አልተፈለገ ህይወት ከሚመሩ ድርጊቶች መከላከል ያስፈልጋል፤ ይህን ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

በቻቺ ከለሚ ኩራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review