ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባትና የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገርባት የሰፊ ባህል ባለቤት ነች።በደም ተሳስረው ለዘመናት አብረው የኖሩት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቻቸውን አክብረው ዛሬም በፍቅርና በመከባበር ይኖራሉ።
ብዝሀነትን አክብራ በምትኖር እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሀገር የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ፍቅርና ወንድማማችነትን ፣ መቻቻልና አንድነትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ተፈጥሯአዊ ባህሪያቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ለአንዱ ባህልና እሴት እውቅና መስጠት የሁሉንም ህዝቦች ባህል እንዲጎለብትና የህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑ መገንዘብ ይገባል።
የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ አያሌ ባህሎችና ልማዶች ያሉባት ከመሆኗም ባለፈ አንዱ ብሄረሰብ የሌላውን ብሄረሰብ ባህል እያከበረ እርስ በእርስ በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ነች።
የህዝቦች መተዋወቅ ለብሄራዊ አንድነትና መግባባት ለመፍጠር ያለው እገዛ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ትውውቅን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መፈቃቀድን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን የሚያጎለብት በመሆኑ ይህንን ማጠናከርና ማህበራዊ አንድነታችንን ማስቀጠል ይገባል።
ለአብነትም የሸዋል ዒድ በዓል ከበዓልነቱ ባሻገር የሀረሪ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እሴቶች መገለጫ ነው። የሸዋል ዒድ በዓል ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ከነሙሉ ክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ደማቅና እንደ ሌሎች በዓላት ሁሉ የኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ባህላዊ ዕሴታችን ነው።
በመሆኑም ዛሬ ላይ በዓሉ የሀረሪ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ከዚያም አልፎ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሃብት ሆኖ ይገኛል።
ክብር ለቀደምት አባትና እናቶቻችን ይግባቸውና ይህንን የመሰለና ለአገራችን እንደ ውብ ፈርጥ አምረውና ጎልተው ከሚታዩ በዓላት አንዱ የሆነውን ይህንን ባህላዊ ዕሴት ለዚህ ትውልድ እንዲደርስ አድርገዋል።
የሹዋሊድ ምሽት ሀረር የምትታወቅበት የአብሮነት እሴትም ጎልቶ የሚታይበት የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችም በጋራ የሚሳተፉበት ባህላዊ ክብረ በአል ነው።
የሹዋሊድ ክብረ በዓል የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት በመሆን በክልሉ በሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች በሚኖሩ ህዝቦች ጭምር በጋራ በአንድነት የሚከበር በመሆኑ ከነሙሉ ክብሩና ለዛው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር መላው ኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ አደራችንን በአግባቡ መወጣት መቻል ይኖርብናል።