
AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው 41 የአእምሮ ሁኔታን በተለይም የሚጥል በሽታ ለመለየት እና ሌሎች የአእምሮ ችግሮችን ለመመርመር የሚችል የህክምና መሳሪያ (EEG) በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙ 7 ሆስፒታሎች በዛሬው እለት በስጦታ ለግሰዋል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ፤ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የተለያዩ ሆስፒታል ዳይሬክተሮች በተገኙበት ነው ስጦታውን ያበረከቱት፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ከሚሰራቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ማሳደግ፣ ጥራቱንና ተደራሽነቱን የጠበቀ የህክምና እና ክብካቤ አገልግሎት እንዲሰጥ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መሆኑም ተወስቷል፡፡
በመሆኑም ጽ/ቤቱ በዚህ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን በመሰራት ላይ እንደሚገኝና ከዚህ በፊትም ለአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ለጎንደር ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት መረጃ አስታውሷል፡፡
በዛሬው እለት የተደረገው ይህ ከፍተኛ ድጋፍም ሆስፒታሎቹ እየሰጡ ያለውን የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የተደገፈ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል፡፡