AMN-የካቲት 10/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን እና አሴት ግሪን ለተቀናጀ የወተት እና የእርሻ ልማት ፕሮጀክት 600 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የባለ ድርሻዎች ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ በከፍተኛ የንግድ ኢንቨስትመንት ለመለወጥ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ የጋራ ቁርጠኝነትን ያሳያል ተብሏል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር በተገኙበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም እንዲሁም የአሴት ግሪን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር አፍሺን አፍሻርኔጃድ ስምምነቱን ፈፅመዋል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚተገበር ሲሆን 600 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ይደረግበታል ነው የተባለው።
የመጀመርያው ምዕራፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወተት እርባታና ማቀነባበሪያ ሥራን የሚቋቋም ሲሆን 60 በመቶው ቀጥታ ወደውጭ የሚላክ ይሆናል።40 በመቶው ደግሞ ለሀገር ውስጥ የሚውል መሆኑ ተመላክቷል። ይህም የተቀናጀ ቀጣይነት ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲኖር እንደሚያስችል ተገልጿል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የቅባት እህሎችን፣ ጥጥና ሩዝ የማምረት ስራዎች የሚከናወኑበት ሲሆን በላቁ የማቀነባበሪያ ፋሲሊቲዎች እና በተዋሃደ የአምራቾች የድጋፍ ማእከል እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በሄለን ጀንበሬ