
AMN ኅዳር -30/2017 ዓ.ም
በሀገራት መካከል የሚደረግ የሀይል ትስስር በየሀገራቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት መሆኑን የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ አመለከቱ ፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር (East African Power pool) የሚኒስትሮች ስብሰባ በሞምባሳ፣ ኬኒያ እየተካሄደ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በሀገራት መካከል የሚደረግ የሀይል ትስስር በየሀገራቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በቀጠናው የሚፈጠረው የሀይል ትስስር የታዳሽ ሀይል ልማትን በስፋት ለማከናወንና በቀጠናው ዘላቂነት ያለው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ንጹህ ኢነርጂ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በማከልም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ የሀይል ትስስሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የአለም ባንክና ሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያከናወነች የሚገኘው የሀይል ትስስር ለሌሎች አካባቢዎች ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር (East African Power pool) እ.ኤ.አ. 2025 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ተቋሙ ስራ ሙሉ በሙሉ እንደሚጀምር በአበል ሀገራት መካከል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ለኬኒያ፣ እና ለሱዳን ሀይል በማቅረብ ላይ የምትገኝ ሲሆም፤ በቀጣይም ለደቡብ ሱዳን እና ለታንዛንያ ሀይል ለማቅረብ በሂደት ላይ እንደምትገኝ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡