በኡዝቤኪስታን ታሽኬንት ከተማ እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፍ ፓርላማ ህብረት ስብሰባ በዓለም አቀፍዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የኢትዮጵያን መልካም ልምድና ተሞክሮ ማስተዋወቅ መቻሉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ስብሰባው በዓለም ዙሪያ ያሉ የፓርላማ አመራሮችና አባላት እየተገናኙ በዓለም አንገብጋቢ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚመክሩበትና የተለያዩ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፉበት የጋራ መድረክ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስፍረዋል።
ስለ ዴሞክራሲና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣ ሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመሳሰሉ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ውይይት፣ ምክክር እና የሀገራት አቋም የሚገለጽበት የጋራ መድረክ ነው ብለዋል።
በመድረኩ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢዮጵያ ልዑክ ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የኢትዮጵያን መልካም ልምድና ተሞክሮ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተዋወቅ መቻሉን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞዋን እውን ለማድረግ እያከናወነች ያለውን የፖለቲካ የኢኮኖሚና ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች ከዓለም አቀፉ ዘለቂ የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም ፈጣንና ተከታታይ እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ በጉባዔው ላይ መነሳቱን ነው የገለጹት።