በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ2 ሺህ 300 ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ

You are currently viewing በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ2 ሺህ 300 ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ

AMN – ጥር 19/2017 ዓ.ም

በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ2 ሺህ 300 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ስሙ ሰንጋ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

መንግስት የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በህጋዊ መንገድ እንዲደረግና ግብይቱም በቴሌ ብር ብቻ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ይሁንና አንዳንድ ግለሰቦች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ታሳቢ በማድረግ በህገ-ወጥ መንገድ ግብይት በመፈፀም ህጋዊ የግብይት ሰንሰለቱን ወደ ጎን በመተው የሀገር ሀብት የሆነውን ነዳጅ በማሸሽ በውድ ዋጋ ለመሸጥ ሲታትሩ ይስተዋላል።

ይህንን ችግር ለመፍታት ፖሊስ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን የዚሁ ስራ አካል የሆነው የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል በህገ-ወጥ መንገድ በአንድ ኮንቴነር ውስጥ በጀሪካን ተሸሽጎ የነበረ 2ሺህ 360 ሊትር ቤንዚል ከሁለት ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ግለሰቦቹ መንግስት ያወጣውን የነዳጅ መመሪያ በመተላለፍ የሀገር ሀብት የሆነውን ነዳጅ በህገ-ወጥ መንገድ ሊሸጡ ሲሉ መያዛቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

ህብረተሰቡ በመሰል የወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥም የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review