
AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም
በመርካቶ ሸራ ተራ አካባቢ በገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ ስም ሲያጭበረብር የነበረ ግለሰብ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ ።
በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ጋር ባካሄደው ቅንጅታዊ ክትትል የቢሮ ሰራተኛ በመምሰል ነጋዴዎችን ሲያጭበረብር የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተመልክቷል።
ቢሮው ከህዳር 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፌደራል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ያለደረሰኝ ሽያጭ ላይ ቁጥጥር መጀመሩ ይታወቃል ።
ይህን መነሻ በማድረግ በህግ ቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ግለሰብ በመርካቶ ገበያ በአንድ ግለሰብ ሱቅ ውስጥ በመግባት የዕቃዎች ደረሰኝ ሲጠይቅና ሲያጭበረብር በደረሰ ጥቆማ መሠረት ለማምለጥ ቢሞክርም በፓሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል ።
ቢሮው የንግዱ ማህበረሰብ ማንኛውም በግል ወይም በቡድን የሚንቀሳቀሱ አጭበርባሪዎች ወደ ንግድ ስፍራቸው ሲመጡ የቢሮ ሰራተኛ መሆናቸውን መታወቂያና መለያ ባጅ በመጠየቅ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ተጠቁሟል ።
ከዚህም በተጨማሪ አጠራጣሪ ድርጊቶች ሲያጋጥሙት በነፃ የስልክ መስመር 7075 በመጠቀም እንዲጠቁም ጥሪ መተላለፉን ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።