የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ሁሉን አቀፍ የመንግስት ድጋፍ በመጠቀም ሀብት ማፍራት ለቻሉ ከ281 በላይ የ13ተኛ ዙር ተመራቂ ኢንተር ፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ የመማሸጋገር መርሀ ግብር እያካሄደ ይገኛል፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍና ወደ መካከለኛ ደረጃ ኢንተርፕራይዝ ማሸጋገር የአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ መሰረት የሚጥል መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ክህሎት መር የስራ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና በማበረታታት ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ በትኩረት እየሰራ እንደሆነና የዛሬው መርሃ ግብርም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩት በዘጠኝ መስፈረቶች ተመዝነው ሲሆን፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ያላቸው የሀብት መጠን፣ ትርፋማነት፣ የገበያ መጠን እና ሌሎች መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በዚህም ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ከ281 በላይ ኢንተርፕራይዞችን ማስመረቅ እንደተቻለ አንስተዋል፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ደረጃ ኢንተርፕራይዝ ማሸጋገር የአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ መሰረት የሚጥል መሆኑን ያነሱት ሀላፊው፣ ይህም የውጪን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ዓላማ የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡
የፍይናንስ ድጋፍ፣ አቅም ግንባታ ስልጠና፣ የገበያ ትስስር፣ የቦታና የመሰረት ልማት ጨምሮ በርካታ ድጋፍ ስለመደረጉ ያነሱት ሀላፊው ይህንን በመጠቀም በቀጣይ ጊዚያት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ የኢንተርፕራይዞች ቀጣይ የቤት ስራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በራሄል አበበ