በአዲስ አበባ ከተማ በዓላትና ሰርግን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጽሙ መንገድ የሚዘጉ አሽከርካሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
ሕብረተሰቡ የጸጥታ አካላት የሚያስተላልፉትን የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክቶች በአግባቡ እየተገበረ መሆኑን ተከትሎ በከተማዋ የወንጀል ድርጊቶች እየቀነሱ መምጣታቸውንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንዳሉት፣ በከተማዋ የትንሳኤ በዓል በሰላማዊ ሁኔታ ተከብሯል።
ቀላል ከሚባሉ የስርቆትና የማጭበርበር ድርጊቶች ውጪ በዓሉን ተከትሎ ውስብስብና ከባድ የወንጀል ድርጊቶች አለመፈጸማቸውንም አመልክተዋል።
ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበሩ መሆኑን በመጥቀስ።
መጪውን የሰርግ ወራት ተከትሎ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ላይ ያልተገባ የመንገድ መጨናነቅ የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ከተማዋን በማይመጥን መልኩ መንገድ በሚዘጉና የትራፊክ ፍሰቱን በሚያስተጓጉሉ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢው የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።