በመዲናዋ በከተማ ግብርና ከለሙ ሰብሎች 75 በመቶ መሰብሰብ ተችሏል

AMN – ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ከለሙ ሰብሎች ለመሰብሰብ ከተያዘው ዕቅድ እስከ አሁን 75 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን በከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የሰብል ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ኪዳነማሪያም ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ የቀረውን 25 በመቶ የደረሱ ሰብሎች የመሰብሰብ ሥራ እስከ ታኅሣሥ 30 ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 34 ወረዳዎች በመኸር እርሻ 6 ሺህ 835 ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ፤ 7 ሺህ 165 ሔክታር መሬት ጤፍ እና ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑንም አመላክተዋል።

በኮሚሽኑ በ2016/17 የምርት ዘመን ከመኸር እርሻ 177 ሺህ 653.6 ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደነበር ያነሱት ባለሙያው፣ አሁን ባለው ግምገማ መሠረት ከ179 ሺህ 800 ኩንታል በላይ እንደሚሰበሰብ እና ይህም ከ2 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ይህን ያክል ሔክታር መሬት ማልማት የተቻለውም “ማንኛውም ክፍት መሬት ፆም ማደር የለበትም” የሚለውን መርሕ በመከተል በተከናወነ ሥራ ተቋማት የምርት ማዕከል እንዲሆኑ ታስቦ በመሠራቱ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ብዛት ያላቸው ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ኮንዶሚኒየም አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ ግቢዎችን ለእርሻ ሥራ በማዘጋጀት ሰፊ ሔክታር መሬት ማግኘት እንደተቻለም ተናግረዋል።

የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰቡ እንቅስቃሴም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ያነሱት ባለሙያው፤ በተለይም አጠቃላይ የከተማው የወጣቶች ሊግ በየክፍለ ከተማው በመሳተፍ ከብክነት የፀዳ የምርት አሰባሰብ ላይ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ አጠቃላይም የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የከተማ ግብርና ሥራ ላይ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ በመጀመር አርሶ አደሩን በስፋት አያሳተፈ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በመሆኑም ከ507 ሺህ በላይ ነባር አርሶ አደሮችን በዕፅዋት ሀብት ልማት ታቅፈው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ያነሱ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ደግሞ 114 ሺህ አዳዲስ አርሶ አደሮችን ለማስገባት ዕቅድ ተይዞ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review