በመዲናዋ አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት መኖሩና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት መኖሩና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ተገለጸ

AMN- ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ መሆኑና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዦች፣ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ገምግመዋል።

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በተሽከርካሪ ስርቆት፣ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር የተገኙ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነስቷል፡፡

እንዲሁም በበርካታ ሞባይል፣ ላፕቶፕ፣ ኮምፒዩተሮች፣ በስፖኪዮ፣ በጎማ እና በሌሎች የመኪና መለዋወጫዎች ስርቆት የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንዲሁም የአይ ኤም ኢ አይ ማጥፊያ ማሽን ተጠቅመው የተሰረቁ ሞባይሎች እንዳይገኙ የሚያደርጉ፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ዝርፊያ የሚፈፀሙ እና በርካታ ሽሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን ይዘው የተገኙ ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ታውቋል።

በተለይም በቂርቆስና በቦሌ ክፍለ ከተሞች በቅንጅት በተካሄደ ልዩ ኦፕሬሽን ተደራጅተው በመንግስት መሠረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ፣ በሞተር ሳይክል ሞባይል የሚነጥቁ፣ 12 የኤ ቲ ኤም ካርድ ከግለሰቦች በማታለል ወስዶ ገንዘብ የዘረፈ ተጠርጣሪ ግለሰብን ጨምሮ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸዉ በምርመራ እየተጣራ መሆነ ተገልጿል፡፡

በተካሄደው ኦፕሬሽን የከተማዋ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ መሆኑንና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ በግምገማው ላይ ተገልጿል።

አዲስ አበባ ከተማን ፀጥታ እና ደኅንነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እና የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያደገ መሆኑን በግምገማው ተነስቷል፡፡

የጋራ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በኦፕሬሽኑ የተገኙ ውጤችም እየተገመገሙ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ መመላከቱን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review