በአዲስ አበባ የወረቀት መታወቂያን የቀየሩ እና በምትኩ የብሄራዊ መታወቂያን (ፋይዳ) የያዙ ዜጎች ቁጥር ሁለት ሚሊየን መሻገሩን የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የሲቪል ምዝገባ እና የመታወቂያ ስርዓትን መነሻ አድርገው ከሚዘጋጁ ኮንፍረንሶች ትልቁ የሆነውን ‹‹አይ ዲ ፎር አፍሪካ›› ጉባኤን፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ኬፕታውን በተካሄደው ውድድር ላይ አሸናፊ ሆና የዘንድሮውን ኮንፍረንስ አዘጋጅታለች፡፡
መዲናዋ ይህንን አለም አቀፋዊ ሁነት እንድታሰናዳ ያስቻላትን አዎንታዊ ገጽታ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከውሎ አዲስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያብራሩት፤የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ፤ በተለይም ዲጂታል ትራንስፈርሜሽን እያመጣ ያለው ለውጥ እንዲሁም ብሄራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ላይ የተሰሩ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደው የሁለቱም ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለከተማዋ ውብ ገጽታን ከማላበሳቸውም ባሻገር አለም አቀፋዊ ኮንፍረንሶች እንዲዘጋጁባት የሚያስችላትን ምቹ መደላድል በመፈጠሩ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማደጉን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የወረቀት መታወቂያን የቀየሩና በምትኩ የብሄራዊ መታወቂያን (ፋይዳ) የያዙ ዜጎች ቁጥር ሁለት ሚሊየን መሻገሩንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ስማርት ሲቲን እውን ከማድረግ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎችን ከማሳለጥ አንጻር ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ታላላቅ አለም አቀፋዊ አህጉራዊ እና መሰል ሁነቶችን በማስተናገድ የምትታወቀው አዲስ አበባም እያስተናገደች በሚገኘው የአይ ዲ ፎር አፍሪካ 11ኛው ጉባዔ ላይም በወሳኝ ኩነትና በፋይዳ ምዝገባ ቅንጅታዊ ትግበራ ላይ ልምዷን አጋርታለች፡፡
በትባረክ ኢሳያስ