በመጪው የትንሳዔ በዓል የሚያጋጥምን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
AMN – ሚያዚያ 09/2017 ዓ.ም
በመጪው የትንሳዔ በዓል የሚያጋጥምን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቁ፡፡
በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኃይል መቆራረጥ እና መዋዠቅ ችግር እንዳይፈጠር፣ ከተከሰተም አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብረ-ሃይል በየደረጃው በማዋቀር ወደ ስራ መገባቱን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
ግብረ-ሃይሉም በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ-ጥገና ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
ሆኖም መሰል ዝግጅቶች ቢደረጉም የሃይል መቆራረጥ ችግር በከፊልም ቢሆን ሊያጋጥም ስለሚችል የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ባሉት ጊዜያት ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም አገልግሎቱ አሳስቧል፡፡
ድንገት የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም ወይም ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘትና ለመስጠት በ905 እና በ904 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻል አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡