በምስራቅ ሐረርጌ በደኖ ወረዳ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አካባቢው ወደ ቀደመ የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲመለስ እየረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በወረዳው በተከናወነው በዚህ የልማት ስራ ተራሮች አረንጓዴ እየለበሱ፣ምንጮችም እየተመለሱ መሆኑ ተመላክቷል።
በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የበደኖ ወረዳ አስታዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ዪዬ በተፋሰስ ስራዉ በለሙ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የተፋሰስ ስራው በማህበረሰቡ ተነሳሽነት በከፍተኛ ትጋት የተከናወነ መሆኑ አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
የተፋሰስ ስራውን ተከትሎ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ የልማት ስራው ከተጀመረ ወዲህ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው፣ አሁንም ቀሪ አካባቢዎችን ለማልማት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሀብታሙ ሙለታ