AMN – ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም
በሲዳማ ክልል ውሃ አጠር ስምንት ወረዳዎች የክረምት ውሃን አገልግሎት ላይ ማዋል የሚያስችል ግድብ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን የሲዳማ ክልል መስኖ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በክልሉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ጉብኝት እያደረጉ ነው።
የክልሉ መስኖ ልማት ኤጀንሲ እንዳለው ጥናቱ በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ይገባል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይ ክልሉ አሁን ላይ እስከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመበጀት የተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታትም 26 ወንዞችን በመጥለፍ እና በከርሰ ምድር ውሃ ደግሞ አምስት ጉድጓዶችን የማልማት ስራ ስለመከናወኑም ነው የጠቀሱት።

በዚህም እንደ ክልሉ በቲማቲም’ ሀባብ ‘ፎሶሊያ’ ቀይ ሽንኩርትና ሌሎችም ክላስተሮች 5 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ደግሞ ከ7 ሺህ በላይ አርሷደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለፁት።
በክልሉ የከርሰ ምድር ውሃ እና የወንዞች አጠር በሆኑት ስምንት ወረዳዎች በክረምት ውሃን በመያዝ መጠቀም የሚቻልበት የግድብ ስራ ጥናት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
በክልሉ ሰፋፊ የመስኖ ልማት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜናዊ ሲዳማ ክልል ዞንም ከ18 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አንደሚለማ ተገልጿል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ እና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ፎላ በ145 ክላስተሮች ከ70 በላይ አርሷደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሮቹ ቁጥር እስከ መጪው ጥር ወር ከ126 ሺህ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።
በበጋ ስንዴም በዞኑ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
በአፈወርቅ አለሙ