በሸሪአ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው

AMN-ኅዳር 22/2017 ዓ.ም

በሸሪአ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የፍትህ አገልግሎት ጥራት ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።

በሸሪአ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ሸሪአ ፍርድ ቤት በጋራ ያዘጋጁት ረቂቅ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፥ በሕገ መንግስት አንቀጽ 34 የጋብቻ፣ የቤተሰብና የግል መብቶች ላይ የሚነሱ የሕግ ጉዳዮችን በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ በሸሪአ ፍርድ ቤት የመዳኘት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 78(5) ድንጋጌ መሠረት ባህላዊና ሐይማኖታዊ የሙግት መፍቻ መንገዶች እውቅና እንደሚሰጣቸው መመላከቱን አስረድተዋል፡፡

የሸሪአ ፍርድ ቤቶችም የዚህ ሕገ መንግስታዊ እውቅና መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸው፥ በአማራጭ የሙግት መፍቻ መድረክነት እያገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የሸሪአ ፍርድ ቤት ተገልጋዮችን ከማርካት አንጸር ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ከሚቀርቡ ቅሬታዎች በተጨማሪ በጥናት መለየቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ችግሮቹን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት የተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ ያሉ ድክመቶችን ለማሻሻል ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የሸሪአ የህግ ስርዓት የመደበኛ የፍትህ ስርዓቱን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሀገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሠረት አሰራሮችን በማሻሻል የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የፍርድ ቤቶቹን ችግር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ታሪካዊና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

የጥናት ቡድን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፤ የሸሪአ ህጉ በውርስ፣ በጋብቻና በቤተሰብ ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮችን ብቻ የማየት ስልጣን እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢኮኖሚና ሌሎች ጉዳዮችን የማየት ስልጣን፤የዳኞች ሹመት፣የትምህርት ደረጃና ተጠሪነት መሻሻል ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ጠቅሰዋል፡፡

የተዘጋጀው ጥናት እነዚህና መሰል ጉዳዮችን በማሻሻል በሸሪአ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠው የፍትህ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት አወንታዊ ምላሽ አግኝቶ የፍርድ ቤቶቹን አቅም ለማጠናከር ጥናቱ በእጅጉ እንደሚያግዝም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review