በሻኪሶ ከተማ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሆስፒታል ለአገልግሎት በቃ

You are currently viewing በሻኪሶ ከተማ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሆስፒታል ለአገልግሎት በቃ

AMN – መጋቢት 27/2017 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል ሻኪሶ ከተማ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ ግልጋሎት እንዲሰጥ የተገነባው ሆስፒታል የግንባታ ወጪው የተሸፈነው በሜድሮክ ኩባንያ ነው።

በሆስፒታሉ ምረቃ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ ዶክተር ታየ ታሪኩ፤ ሆስፒታሉ በአካባቢው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።

ሆስፒታሉ ህክምና መስጠት የሚያስችል አልጋና መድሀኒትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉለት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሜድሮክ ኩባንያ ከሆስፒታሉ ግንባታ ባለፈ የሻኪሶ ከተማና አካባቢውን ህዝብ በመጠጥ ውሀ፣ በትምህርትና በመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው የሆስፒታሉ አጠቃላይ ግንባታ ወጪ 450 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታውሰዋል።

ሆስፒታሉን በዘመኑ ቴክኖሎጂ እና በሰው ሀይል የማሟላት ስራ እንደሚቀጥል ገልጸው ለሻኪሶ ከተማና አካባቢውን ህዝብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሆስፒታሉን ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ አጠቃላይ ደረጃ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አባገዳ ገናሌ አጋ፤ ለአመታት የዘለቀው የሆስፒታል ጥያቄ በመመለሱ ሁላችንም ተደስተናል ብለዋል።

እናቶች ሲወልዱና ሲታመሙ አዶላ፣ ነገሌ ቦረና እና ይርጋለም ሆስፒታሎች ድረስ በመሄድ ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው ለኩባንያው ምስጋና ማቅረባቸውን ተነግሯል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ቦጋለች ጅሎ በበኩላቸው በሆስፒታሉ መገንባት የአመታት ጥያቄያችን ዛሬ ተመልሶልናል ብለዋል።

ሆስፒታሉ በተለይም ለእናቶች እና ህጻናት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ወይዘሮ ቦጋለች ከዚህ ቀደም አዶላ አሊያም ነገሌ ቦረና ሆስፒታል ድረስ ለመሄድ መናገራቸውን የዘገበው ኢዚኣ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review