AMN-ታህሣሥ 16/2017 ዓ.ም
የፊንላንድ ሞተር አምራች ኩባንያ ያመረተው (Wärtsilä-Sulzer RTA96-C) የተሰኘው ባለ ሁለት ስትሮክ እና 14 ሲሊንደር ያለው ግዙፉ የናፍታ ሞተር፣ ኮንቴይነር ጫኝ ግዙፍ መርከቦችን እንዲያንቀሳቅስ ታስቦ መነደፉ ተገልጿል፡፡
አሥራ ሦስት ሜትር ከፍታ፣ ሃያ ስድስት ሜትር ርዝመት እና 2 ሺህ 300 ቶን ወይም 2 ሚሊዮን 300 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ግዙፍ ሞተር እስከ ዛሬ ከተገነቡት ሁሉ ትልቁ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡
የሞተሩ ክራንክሻፍት ብቻ 300 ሺህ ኪሎ ግራም ሲመዝን፣ 14ቱ ፒስተኖች እያንዳንዳቸው ደግሞ 5 ሺህ ኪሎ ግራም እንደሚመዝኑ ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ያለው ሞተሩ፣ 80 ሺህ 80 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ በቀን 250 ቶን ወይም 250 ሺህ ሊትር ከባድ ነዳጅ እንደሚጠቀም ተመላክቷል፡፡
የሞተር አምራች ኩባንያው የዓለም ግዙፉን ሞተር ለማምረት ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ ቀደም ብሎ ያመረተው ባለ 12 ሲሊንደር ሞተር ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦችን ለማንቀሳቀስ በቂ እንዳልሆነ በማረጋገጡ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ባለ 14 ሲሊንደር እና ባለ ሁለት ስትሮኩ (Wärtsilä-Sulzer RTA96-C) የተሰኘው የመርከብ ሞተር በፈረንጆቹ 2006 የተመረተ ሲሆን፣ በዛው ዓመት ገበያ ላይ መዋሉም ተመላክቷል፡፡
እንደዚህ አይነት ትልቅ እና ውስብስብ ሞተር መገንባት በጣም አስቸጋሪ እና የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱም ከባድ በመሆኑ፣ ከ 25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መጠየቁ ምንም አያስደንቅም መባሉን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያመላክታል፡፡