AMN – መጋቢት 6/2017 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ ደህንቱ የተጠበቀ የበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) አጠቃቀም ቀን “ደህንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀምን ለታዳጊ ሕፃናት በማስተማር ትውልድን እናስቀጥል!” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ተከብሯል።
በመድረኩ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን፣ በችግሩ እና መፍትሄው ዙሪያ ለመምከር ያለመ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።
የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በበይነ መረብ በታገዘ መልኩ በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የህፃናትን የኢንተርኔት አጠቃቀም ክህሎት ማዳበር እና ደህንነቱ የተጠበቀ የአጠቃቀም ስርዓት ልምድን እንዲያዳብሩ መስራት፣ መልካም አጋጣሚዎችንና ያለውንም ተፅእኖ መረዳት እንዲችሉ ማብቃት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ወላጆች የልጆቻቸውን የኢንተርኔት አጠቃቀም በተቻለ መጠን መከታተል፣ በገጠመኞቻቸው ዙሪያ ግልጽ ውይይትና መግባባት መፍጠር፣ በተቻለ መጠንም የአጠቃቀም ደንብ እንዲኖር ማስቻል ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት እና የኢንተርኔት ተደራሽነት እየታየ በመምጣቱ የዲጂታል ከባቢው አካታች፣ ለህፃናት ምቹ እና ከደህንነት ስጋት ነፃ እንዲሆን ጠንካራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በበይነ መረብ በታገዘ መልኩ በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም አካል የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የዩኒሲፍ የህፃናት ጥበቃ ሀላፊ ጆላንዳ ቫን በበኩላቸው፣ ህፃናት በብይነመረብ ለፆታዊ ጥቃት እየተጋለጡ በመሆኑ ታዳጊ ህፃናትን ከኢንተርኔት ጥቃት ለመጠበቅ በጋራ መሰራት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።