በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ህዝብን የሰላም ባለቤት ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ህዝብን የሰላም ባለቤት ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- የካቲት 12/2017 ዓ.ም

በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ህዝብን የሰላም ባለቤት ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉባኤው ባቀረቡት ሪፖርት፣ህዝቡ በሰላም ሰራዊት ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የመከላከል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ከፌዴራል እና ከአጎራባች ከተሞች ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠርም የወንጀል እና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል፣ ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ከህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ከኢኮኖሚ አሻጥር፣ ከዝርፊያ፣ ከሽብር እና ደረቅ ወንጀሎች ጋር የተያያዙ ከ4 ሺህ 687 በላይ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የመከላከልና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል፡፡

በዚህም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ እና ከትምህርት ተቋማት ውጭ የሚገኙ እና ለጸጥታ ስጋት በሆኑ 2 ሺህ 919 አዋኪ ድርጊቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ ውጤታማ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ የወንጀል ምጣኔ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የደንብ መተላለፍ እና ተያያዥ ህገ-ወጥ ተግባራትን በመከታተል፣ በመቆጣጠር እና እርምጃ ከመውሰድ አንፃር 2 ሺህ 464 ህገ-ወጥ ግንባታዎች ላይ፣ 108 ህገ-ወጥ ንግድን፣ ህገ-ወጥ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን መቆጣጠር እና ደንብ ማስከበር እንደተቻለም ተናግረዋል።

በፍትህ ስርዓታችን ከህግ የበላይነት አንፃር በፍትሐብሔር ጉዳዮች በፍርድ ቤት የመርታት ዐቅም በግማሽ ዓመቱ ከ94.25 በመቶ ወደ 95 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክርክር ከተደረገባቸው 4 ሺህ 741 መዝገቦች ውስጥ በ1ሺህ 895 የፍትሐብሄር መዝገቦች ላይ ውሳኔ እንደተሰጠ እና ከዚህ ውስጥም 1ሺህ 766 መዝገቦች ለመንግስት ሲወሰን በ129 መዝገቦች በመንግስት ላይ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ለመንግስት በተወሰነባቸው መዝገቦች በገንዘብ ከ 1. 7 ቢሊየን በላይ ብር፣ በዓይነት ደግሞ 217 ቤቶች፣ 12 ሼዶች እንዲሁም 143.2 ሄክታር መሬት የመንግስት እና ሕዝብ ጥቅም ማስጠበቅ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review