AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
በበጀት ዓመቱ መንግስት 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዶ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም እየታዩ ካሉ አፈፃጸሞች አንፃር ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳካት እንደሚቻል ይጠበቃል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀምን መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግስት የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ማዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ዕቅድም በየደረጃው የ5፣ የ1 ዓመት በየሴክተሩ እና ተቋማቱ ደግሞ ከዛ ባነሰ ጊዜ የተግባር ዕቅድ ተዘጋጅቶ እነዚያን በሚገባ አሰናስሎ በማሳከት ትልቁን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ጉጉት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያለፈው ዓመት ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት 4.2 በመቶ እንደሚሆን ገምተው እንደ ነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሁንና ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 8.1 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመትም ከሰሃራ በታች ላሉ ሀገራት የተሰጠው የኢኮኖሚ ዕድገት ግምት ከአምናው የራቀ እንዳልሆነ በመጥቀስ ነገር ግን ኢትዮጵያ 8.4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳ ይህንንም ለመተግበር ጥረት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ያለፉት ስምንት ወራት አመርቂ የኢኮኖሚ እድገት አፈፃጸሞች መኖራቸውን እንደሚያመላክቱ በማንሳትም፣ በቀጣይ አራት ወራት ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ፣ በዘንድሮ ዓመት ከታቀደው ከ8.4 በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
ባለፉት 8 ወራት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመላከቱት፡፡
በግብርናው ዘርፍ ምርትን ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የስንዴ አምራች ሀገር መሆን እንደቻለች ተናግረዋል፡፡
የቡና ምርታማነት እና የወጪ ንግድን በተመለከተም በለውጡ ማግስት 700 ሚሊየን ዶላር ገደማ በዓመት ይደረግ ከነበረበት ባለፉት 8 ወራት ብቻ ከ1.2 ቢሊየን ዶላር በላይ ወደውጭ መላክ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው