AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቡልቡላ 40/60 እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት መቆጣጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታዉቋል።
የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለ ኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ የእሳት አደጋው ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ አካባቢ ነው የተከሰተው።
በአካባቢው በሚገኘው በአንድ ጅምር ሕንጻ ግራውንድ ላይ የተከማቸ የሕንጻ መሳሪያ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ላይ የእሳት አደጋ አጋጥሞ እንደነበረም ነው የገለጹት።
እሳቱን ለማጥፋት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ እሳቱ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዛመት በማድረግ መቆጣጠር መቻሉም ተገልጿል፡፡
የእሳት አደጋውን ለማጥፋት ስድስት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና 2 የውሃ ቦቴ ከ40 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መሰማራቱ ተመላክቷል፡፡
በአደጋው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል።