በተለያየ ጊዜ የተሰበሰበ በርካታ የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች እና አደንዛዥ ዕፆች ተወገዱ

AMN-ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተለያየ ጊዜ የተሰበሰበ በርካታ የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች እና አደንዛዥ ዕፆችን አስወገደ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክፍለ ከተማውን ሠላም ይበልጥ ለማረጋገጥ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከልና ወጣቶችን ወደ ሱስ የሚወስዳቸው ለማስቆም ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ፍስሀ ጀምበሩ እንደተናገሩት ፖሊስ የአካባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ ከሐምሌ 2016 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ በ3 ዙር ብቻ ከ19 ሺህ በላይ የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን እና 215 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።

እነዚህ የሺሻ ዕቃዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ ፖሊስ በህግ አግባብ ባደረገው ፍተሻ በመኖሪያ ቤቶች፣ ፔንሲዮኖች፣ የሌሊት ጭፈራ ቤቶችና በሆቴሎች ውስጥ መገኘታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የወረዳ 3 ሠላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ስንታየሁ ታረቀኝ እና የወረዳው ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ሽፍት ኃላፊ ጌታቸው መራባ እንደገለፁት የአካባቢውን ሠላም ይበልጥ ለማረጋገጥ ከፖሊስ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩና ሺሻ የሚያስጠቅሙና የሚጠቀሙ ህገ ወጥ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

ሰዎችን ወደ ወንጀል ድርጊቶች የሚገፋፉ መንስኤዎችን ከምንጩ ለማድረቅ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ህብረተሰቡ በአካባቢው አዋኪ ድርጊቶችን የሚያስጠቅሙና የሚጠቀሙ ግለሰቦችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review