AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም
ዛሬ በተጀመረው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሞሪታኒያ ፕሬዝደንትና የአፍሪካ ህብረት ተሰናባቹ ሊቀመንበር ሞሃመድ ኡልድ ጋዝዋኒ ንግግር አድርገዋል ፡፡
ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከርና የአባል ሀገራት ልማት በማረጋገጥ ረገድ በአጀንዳ 2063 የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት ህብረቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ፡፡
በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ያጋጠሙ ግጭቶችና እሱንም ተከትሎ የሚታዩ ሰብዓዊ ቀውሶችን በማስወገድ ረገድ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በፍልስጤማውያን ላይ ያጋጠመውን ሰብአዊ ቀውስ እንደ ማሳያ የጠቀሱት ሊቀመንበሩ በአፍሪካ ሀገራት እያጋጠመ ያለው ቀውስም ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል ፡፡
የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር የሚጎዱት ረሀብ ፣ ስራ አጥነት ፣የትምህርት እጦት ፣ ደካማ የጤና ስርአት ፣ ሽብርተኝነት እና ደካማ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ዋነኞቹ ችግሮች መሆናቸውንም አመልክተዋል ፡፡
በእነዚህ ችግሮች ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሲታከልበት ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋልም ብለዋል፡፡
የህብረቱን ህግና ስርዓት በመከተል እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ ነው በንግግራቸው ያመለከቱት፡፡
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ግጭቶችን በመነጋገር ለመፍታትና ሰላምን ለማስፈን ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የሰላም እጦትን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ ስራ እንደሚፈልግና ለዚህም በጋራ መስራት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል ፡፡
ሀገራት ለልማት አጀንዳው መሳካት ያላቸውን ሀብት በማስተባበር እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡
የሀይል አቅርቦትን በማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልም ረገድም ሀገራት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በሽመልስ ታደሰ