AMN- የካቲት 20/2017 ዓ.ም
በተቋማት ሪፎርም የላቀ ዲጅታላይዝድ መንገድን የተከተሉ እና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን የተላበሱ ተቋማትን ልምድ እና ተሞክሮ ማስፋት እንደሚገባ የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ ፡፡
ቢሮዉ የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲን ተሞክሮ የሚጋራበት መድረክ እያደረገ ነዉ፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ተቋማት ዘመናዊ አሰራርን የተከተሉ እና ቀልጣፋ አግልግሎትን ለመዲናዋ ነዋሪዎች እንድሰጡ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ሪፎርም ካደረጉ በኋላ ተጨባጭ ለዉጦች ስለመታየታቸዉ ዶክተር ጀማሉ ተናግረዋል፡፡
የተቋማቱን ዘመናዊ አሰራር እና የተሳለጠ ግልጋሎት አሰጣጥ ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ወደ ሌሎች ተቋማት ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ሁለቱ ተቋማት የተጓዙበትን የሪፎርም ሂደት እና የተመዘገቡ ስኬቶች ቀርበዉ ዉይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ተቋማት አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን ልምድ እና ተሞክሮን ይወስዳሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በተመስገን ይመር