AMN- ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም
በተያዘው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
6ኛው የህዝተወካዮች ምክር ቤት ብ 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሠራው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የፋብሪካዎች ውጤታማነት ጨምሯል ብለዋል።
ትልልቅ ፋብሪካዎች ያጋጠማቸውን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋልም ነው ያሉት።
በተደረገው ጥረት ፋብሪካዎች ከኤሌክትሪክ፣ ከቴሌና ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸው ችግር መፈታቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም ከጉምሩክ አሰራር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሥራዎች መጀመራቸውንም አስታውቀዋል ።
በመሆኑም ዘንድሮ 72 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ሥር እንደሚገቡ አመልክተዋል።
ፕሮጀክቶቹም 9 የጨርቃ ጨርቅ፣ 41 የምግብና መጠጥ፣ 4 የኮንስትራክሽንና ኬሚካል ፣15 የቴክኖሎጂ እና 3 ወታደራዊ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ዘንድሮ ማምረት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል ።
ፋብሪካዎቹ በቀጣይ በአፍሪካ ገበያ እያፈላለጉ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያመጡም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው መሥራት እንደማይችሉ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰራው የሪፎርም ሥራ 50 በመቶ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዛቸውን ገልጸዋል ።
ወርቅ፣ ብረታ ብረትና የድንጋይ ከሰል የሚያመርቱ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ነው የተናገሩት።
ከሲሚንቶ ምርት ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአብነት ያነሱት የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ብቻውን በዓመት 450 ሺ ቶን ያመርታል ነው ያሉት። ይህም በዘርፉ 16 በመቶ እድገት ይመዘገባል ብለዋል።
በሲሚንቶው ዘርፍ ለመሰማራት የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህም በጥቅሉ ዘንድሮ እንደ ሀገር ለማስመዝገብ ለታቀደው የ8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ትልቅ ድርሻ እንደሚያበረክት በማብራሪያቸው አስታውቀዋል።
በማሬ ቃጦ