AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ክፍሎች የታዩት ቁስ አካላት ከእይታቸው አኳያ የሳተላይት ወይም የሮኬት ቁርጥራጮች ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ደራሲ፣ የሃይማኖት ምሁር እና የሥነ ፈለክ ባለሙያ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ሕዋው ከምድር ወደ ጠፈር በሚላኩ እና የጠፈር ላይ ተመራማሪዎች በሚጥሏቸው ቁሶች በመቆሸሹ መሰል ክስተቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አስረድተዋል።
ባለፈው በታኅሣሥ 21 ቀን 2017 በኬንያ፣ ሙኩኩ መንደር ውስጥ ከሮኬት የመለያያ ቀለበት በመባል የሚታወቅ አንድ ትልቅ በግምት 2.5 ሜትር ስፋት እና 500 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ብረታማ ነገር መከስከሱንም አስታውሰዋል።
ዶክተር ሮዳስ ለኤኤምኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በምድር ካሉ ሀገራት አንዷ እንደመሆኗ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ክስተቶችን ልታስተናግድ ትችላለች።
በኢትዮጵያ ታሪክ እንዲህ ዓይነት ተፈጥሯዊ አሊያም ሰው ሠራሽ ክስተቶች ተከስተው እንደሚያውቁም ጠቅሰዋል።
ቀደም ባሉ ዘመናት “በዚህ ዘመን ጅራታማ ኮከብ ታየ”፣ “በዚህ ዘመን ፀሐይ ጨለመች”፣ “በዚህ ዘመን ጨረቃ ደም ሆነች” የሚሉ ምዝገባዎች እንደነበሩ ነው ያመለከቱት።
በጥንት ጊዜ ክስተቶቹ ከተከሰቱ በኋላ የመመዝገብ ልምድ እንደነበር በማንሣት፣ አሁን ላይ ሳይንሱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነገሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ የማወቅ እና የመረዳት ዕድል ስለመኖሩም ገልጸዋል።

ከሰማይ ላይ አብርተው ስለሚታዩ እና ስለሚወድቁ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አካላት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ አራት ዓይነት ተፈጥሯዊ የሕዋ ዐለቶች እንዳሉ ገልጸዋል።
እነዚህም አስትሮይድ፣ ሜትዮራይድ፣ ሚትዮር እና ሜትሮይት እንደሚባሉ እና በመካከላቸውም ያለውን መሠረታዊ ልዩነቶች ተንትነዋል።
አስትሮይድ የሚባለው፣ በዋነኛነት በማርስ እና በጁፒተር መካከል ባለው የአስትሮይድ ቀበቶ ውስጥ የሚገኙት ዐለታማ ሥሪት ያላቸው አካላት ሲሆኑ፣ መጠናቸውም 329 ዲያሜትር ያለው ከታናናሾቹ ውስጥ ከ10 ሜትር በታች የሆኑም ይገኙበታል።
ሜትዮራይዶች ደግሞ በሕዋ ያሉ ትናንሽ ዐለቶች ሲሆኑ፣ መጠናቸው ከአሸዋ ቅንጣት እስከ 1 ሜትር አካባቢ የሚደርሱ ናቸው።
አንዳንዶቹ ሜትዮራይድ ዐለቶች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ብረታ ብረት ወይም የድንጋይ እና የብረት ውህዶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ሜትዮራይድ ብዙ ጊዜ ከአስትሮይድ ወይም ከኮሜት ወይም ከሌሎች ፕላኔቶች ጭምር የሚመጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ሚትየር የሚባሉት ደግሞ ሜትዮራይድ ወደ ምድር ከባቢ አየር ወይም ወደ ሌላ ፕላኔት በከፍተኛ ፍጥነት ሲገቡ እና ሲቃጠሉ ሚትየር እንደሚባሉ አብራርተዋል።
ሜትየሮችን “ተወርዋሪ ኮከቦች” ብለን የምንጠራቸው ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ሜትየሮች ከቬኑስ የበለጠ ብሩህ ሆነው ሊታዩ ይችላሉም ብለዋል።
ብዙ ተወርዋሪ ከዋክብት በአንድ ላይ በሰዓታት ሲታዩ “ሜትየር ሻወር” በመባልም እንደሚታወቁ አስረድተዋል።

ሜትሮይት የሚባለው ደግሞ፣ ሳይቃጠል የምድርን ከባቢ አየር አልፎ በምድር ላይ የሚያርፍ የሜትሮይድ ቁራጭ መጠሪያ እንደሆነም አመላክተዋል።
ዶክተር ሮዳስ እንደሚሉት፣ በሰዓት በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ በኃይለኛ ግፊት ወድቆ ሲበታተን ብሩህ ነበልባል ይመስላል።
በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ሜትሮይድ ወደ ምድር ከባቢ አየር ውስጥ የገባው በፈረንጆቹ በ1908 መሆኑን እና ይህም “የቱንጉስካ ክስተት” በመባል እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል።
ይህ ሜትዮር በሩሲያ በሳይቤሪያ ላይ የተከሰተ እንደነበር እና ምድርን ከመንካቱ ጥቂት ማይል ርቀት ላይ መፈንዳቱን ነው የተናገሩት።
የፍንዳታው ኃይልም በመቶዎች የሚቆጠሩ ማይሎች ስፋት ባለው ክልል ውስጥ ዛፎችን ለማውደም የሚያስችል ኃይለኛ እንደነበር ተናግረዋል።
ሌላው በፈረንጆቹ በ2013 በቼልያቢንስክ ሩሲያ ሰማይ ላይ ቤትን የሚያህል ሜትሮይድ በሰከንድ 18 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ከባቢ አየር በመግባት ከመሬት በላይ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መፈንዳቱን አንስተዋል።
ፍንዳታው ወደ 440 ሺህ ቶን የሚገመተውን የቲኤንቲ ኃይል በመልቀቁ ከ518 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ መስኮቶችን የሰባበረ እና ሕንፃዎችን ያበላሽ አስደንጋጭ ሁኔታ እንደፈጠረ ገልጸዋል።
በፍንዳታውም በተከሰተ የመስታወት ስብርባሪ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አብራርተዋል።
በታምራት ቢሻው